ተው እንጂ ፤
ተው እንጂ እሱባለው ፤
ከምን ተነስተህ ነው እኔ እንደማልወድህ የምትናገረው ?
የረባ ባይሆንም ሃሳብ ገብቶኝ ሳለ፤
ልቤ ባንተ መውደድ ካልተንቀዋለለ ፤
መውደድሽ ውሸት ነው ብሎ ነገር አለ?
አንተን ይቅርና የእግዚአብሔር አምሳሉን፣
እንዴት እንደምወደው ረጅም አስፋልቱን ፣
እርግጥ ነው አልክድም ፤
ያስፋልት ያክል ጥቅም ካአንተው አልጠብቅም ፤

አትወጅኝም አትበል

የውሼት መውደድ
አስፋልት ከሚሰበር አንተ ከምትጠፋ
አንተ ብትጠፋ መምረጤ ግልፅ ነው ፤
አስፋልት እስኪጠገን ያለውን መጉላላት እኔ ነኝ የማውቀው ።
እንዲህ አለች ብለህ ጠላችኝ እንዳትል በጣም ነው ምወድህ፤
ከከተማ ጮሌ አፍቅሮ ከሚክድ ትቂት ትበልጣለህ ፤
የከተማ ጮሌ የነቃ የበቃ ትውልድ ስለሆነ ፤
እኔን ከእነሱ እኩል ወደጅኝ ከሆነ፤
ከኔ ባላወራህ ጊዜህ ባልባከነ?
እውነትህን እኮ ነው አራዳ ነኝ ባዩ አፍቅሮ ወይ ወዶ በቶሎ ይክዳል ፤
እንዲያ ሆነ ብዬ ከነሱ በይበልጥ ልወድህ መች ሊቻል?
ዘመኑ ባመጣው አራዳነት ሂሳብ ፤
ፍቅር አይገኝም ወውደድ አይጠገብ፤
በቃል ሲሸነግል እንስቶች ተስበው
ልባቸው ያለውን ማዳመጡን ትተው፤
ሸንጋይ አስመሳዩን ተከትለው ሄደው ፤
ተክደው አያለሁ ፤
እነሱን ተይ ብለህ ምክር ሰጥተኸኛል እቀበልሃለሁ፤
እንጂ እወድሃለሁ ።
እንኳን መካሪየን- ለመብራት ያለኝ የመውደዴ ጥልቀት ፤
ሊገመት አይችልም ፤
በጨለማ ጊዜ የሚሰጠው ደስታ ወደር አይኖረውም ።
ከመብራት አብልጠሽ ውደጅኝ አትልም ብትልም አልሰማህ፤
መብራት ጠፍቶ ሲያድር ያለውን ድንጉርጉር ድብርት የት አይተህ ።
መብራት ከሚጠፋ አንተ ባትኖር በደንብ ደስ ይለኛል ፤
ይሄ እንደምጠላህ በየት በኩል ታይቶ አትወጅኝ ያሰኛል?
እርግጥ ነው አልክድም ፤
አንዲት ሰከንድ እንኳ ናፍቀኸኝ አታውቅም ፤
የፃፍከውን ግጥም ከአንዳንድ ቀን በቀር አንብቤው አላውቅም ።
ይህን አለች ብለህ አትወጅኝም አትበል በኔ ግፍ አትስራ ፤
ኩርፊያህ ዳቦ ላይሰጥ ላይጋግር እንጀራ ።
አንተን ይቅርና የፃፍክልኝን ፁሁፍ አይጣል ስወዳቸው ፤
እቅድ አኑሬአለሁ አንድ ቀን ሲያደርሰኝ በደንብ ላነባቸው።
አትዋሽኝ ካልከኝ ስወድህ ከልቤ በጣም በብዙ ነው፤
"በጣም እወድሃለሁ" ብዬ የፃፍኩት ግን በይኝ ስላልከኝ ነው።
ሳምንት ይቅርና ለዓመታት ብትጥፋ ሳትፅፍልኝ ብትቀር
አትናፍቀኝም ግን እወድሃለሁ ፤
በልብ ያልተፃፈ አይዘልቀውምና ዘንግቼህ እንዳልቀር አትጥፋኝ እላለሁ ።
እሱባለው ቸኮል