መርዝም ፡ መድኀኒት ፡ ነው ፡ ሲሆን ፡ በጠብታ ፡
እንዲሁም ፡ ለተንኰል ፡ አለው ፡ ቦታ ፡ ቦታ ፡
ምን ፡ ቢሠለጥኑ ፡ ቢራቀቁ ፡ በጣም ፡
ሁልጊዜ ፡ ደጋግሞ ፡ ብልጠት ፡ አያዋጣም ፡
በእጅ ፡ የተበተቡት ፡ ተንኰል ፡ ዞሮ ፡ ዞሮ ፡
ማጋለጡ ፡ አይቀርም ፡ እጅና ፡ እግር ፡ አስሮ ።
መጽሐፉም ፡ ይለናል ፡ ሲያስተምር ፡ ጥበብ ፡
ብልጥ ፡ ሁን ፡ እንደ ፡ እባብ ፡ የዋህ ፡ እንደ ፡ ርግብ ፡
ስለዚህ ፡ በብልጠት ፡ ተንኰል ፡ ስትሠሩ ፡
በዝቶ ፡ እንዳይገደላችሁ ፡ ገርነት ፡ ጨምሩ ።
ሁለት ፡ ባልንጀሮች ፡ በጣም ፡ ሲዋደዱ ፡
አንደኛው ፡ በሐሰት ፡ አንደኛው ፡ ከሆዱ ፡
ወስላታው ፡ በሥራው ፡ ሲጠፋ ፡ እየከዳ ፡
ሐቀኛው ፡ ግን ፡ ተርፎ ፡ ሁሉንም ፡ ሲረዳ ፡
ደግና ፡ ክፉን ፡ ሰው ፡ እግዜር ፡ እየለየ ፡
ፍርዱን ፡ በመሬት ፡ ላይ ፡ ይባላል ፡ አሳየ ።
የቅናት ፡ በሽታ ፡ ሕመሙ ፡ የከፋ ፡
የሕሊናን ፡ ዐይኖች ፡ ጨርሶ ፡ የሚያጠፋ ፡
በዚህ ፡ ክፉ ፡ ደዌ ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ ሲለከፍ ፡
የተጣራው ፡ ነገር ፡ ይመስለዋል ፡ ሰፈፍ ፡
ልቡም ፡ እያዳላ ፡ ወደ ፡ ክፋት ፡ ወገን ፡
መሞትን ፡ ይመኛል ፡ ሰውን ፡ ከማመስገን ።
ሕይወት ፡ ጦርነት ፡ ነው ፡ ዋጋህን ፡ የሚያሳይ ፡
መታገል ፡ ግድ ፡ ነው ፡ ስትኖር ፡ ባለም ፡ ላይ ፡
በገዛ ፡ እጁ ፡ ወድቆ ፡ በቁሙ ፡ እየሞተ ፡
መታገል ፡ ያልቻለ ፡ ልቡ ፡ እየታከተ ፡
የሚያገኘው ፡ የለም ፡ በፍቅር ፡ በእርዳታ ፡
በዚች ፡ በመሬት ፡ ላይ ፡ ፍጡር ፡ ካልበረታ ፡
ጥንቱን ፡ አልተሠራም ፡ ለሰነፎች ፡ ቦታ ።
ለይቶ ፡ ለማወቅ ፡ የየሰዉን ፡ ዋጋ ፡
መሆን ፡ ያስፈልጋል ፡ አእምሮው ፡ የረጋ ፡
ባስተዋይነትም ፡ መሆን ፡ ባለጸጋ ።
ሁሉን ፡ በማሻሻል ፡ መጨመር ፡ መቀነስ ፡
የሌለውን ፡ መፍጠር ፡ ያለውንም ፡ ማደስ ፡
መልካሙን ፡ አሰፋፍቶ ፡ መጥፎውን ፡ መደምሰስ ፡
የሚጓዝበትን ፡ ዐቅድ ፡ እያሠመሩ ፡
ከጨለማ ፡ አውጥቶ ፡ ሕዝብን ፡ እየጠሩ ፡
አሳብ ፡ እያቀዱ ፡ ሠርቶ ፡ በማሠራት ፡
ግንባር ፡ ቀደም ፡ ሆኖ ፡ ያስፈልጋል ፡ መምራት ።
የተማረ ፡ ሆኖ ፡ ዕውቀት ፡ እያበራ ፡
የቀሩትን ፡ ሰዎች ፡ በጥበብ ፡ ካልመራ ፡
ጥቅም ፡ የሌለው ፡ ነው ፡ ድካሙ ፡ ኪሳራ ።
ሰው ፡ ሲበድላችሁ ፡ እስቲ ፡ አትናደዱ ፡
ጠላትን ፡ አትጥሉ ፡ ክፉን ፡ ሰው ፡ ውደዱ ፡
የክፉ ፡ ሰው ፡ ክፋት ፡ ጠቃሚ ፡ ነው ፡ ትርፉ ፡
ያነቃቃችኋል ፡ እንዳታንቀላፉ ።
የልቡናው ፡ ስሜት ፡ እየተራቀቀ
ሁልጊዜ ፡ ወደ ፡ ላይ ፡ በጣም ፡ እየላቀ
በሥራ ፡ በጥበብ ፡ ግሎ ፡ ለመነሣት
ቈስቋሽ ፡ ይፈልጋል ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ እንደ ፡ እሳት
ሀብታም ፡ ይደኸያል ፡ ሀኪምም ፡ ይሞታል
ጐበዝ ፡ ይሸነፋል ፡ ብልኅ ፡ ይሳሳታል ፤
የበራውም ፡ ጠፍቶ ፡ የሠሩት ፡ ይፈርሳል ፤
የቆመውም ፡ ወድቆ ፡ የሣቀ ፡ ያለቅሳል ፤
ጌጥም ፡ ሆነ ፡ ጥበብ ፡ ውበት ፡ ሆነ ፡ ክብርም ፤
የማረበት ፡ ነገር ፡ ማስቀየሙ ፡ አይቀርም ።
ፍሬ ፡ መሬት ፡ ወድቆ ፡ ከዋለ ፡ ካደረ
ሰው ፡ ገንዘብ ፡ አግኝቶ ፡ መክበር ፡ ከጀመረ
የመጣ ፡ ነውና ፤ ቀድሞውን ፡ ከጥንት
ሁለቱም ፡ አይድኑ ፡ ከመበላሸት ።
የሰዎችን ፡ ጠባይ ፡ የተመራመረ
ብልኁ ፡ ፈላስፋ ፡ እንዲህ ፡ ተናገረ ፤
በጣም ፡ በማስተዋል ፡ ከላይ ፡ እስከ ፡ ታች ፤
ስመለከታቸው ፡ የሰውን ፡ ልጆች ፤
እያጣሁባቸው ፡ ግብሩ ፡ ሚመሰገን ፤
እንቃቸው ፡ ጀመር ፡ እጅግ ፡ አለመጠን ።
የደንቆሮ ፡ መንፈስ ፡ ምንኛ ፡ ታደለ ፤
ብልጥነት ፡ አላጣም ፡ ጅል ፡ እየመሰለ ፤
እንኳን ፡ መጽሐፍ ፡ ማንበብ ፡ ፊደል ፡ ሳያጠና ፤
ሁሉንም ፡ ያወቀ ፡ ይመስለዋልና ።
የሊቅ ፡ ሰው ፡ መከራ ፡ የብልኅ ፡ አባዜ ፤
ሲጨነቅ ፡ መኖር ፡ ነው ፡ ባሳብ ፡ በትካዜ
አቶ ፡ ዐሳበ ፡ ቢስ ፡ ይተኛል ፡ ዝም ፡ ብሎ
ክትራሱ ፡ ጋራ ፡ ዐሳቡን ፡ ጠቅሎ ።
ኵራትና ፡ ትዕቢት ፡ የሞሉት ፡ አናት፤
ሰይፍና ፡ ጐራዴ ፡ የመቱት ፡ አንገት፤
አይገላገሉም ፡ እንዲህ ፡ በቀላሉ ፤
እመሬት ፡ ላይ ፡ ወድቀው ፡ ሳይንከባለሉ ።
ገንዘብ ፡ መፈጠሩ ፡ ለሰው ፡ አገልጋይ ፤
ሆኖ ፡ ሊሠራበት ፡ አልነበረም ፡ ወይ?
አሁን ፡ ግን ፡ መስገብገብ ፡ በጣም ፡ ሰለበዛ ፤
ሰው ፡ ባሪያ ፡ እየሆነ ፡ ለገንዘብ ፡ ተገዛ ።
ፍጥረት ፡ ደስ ፡ ሲለው ፡ አንተ ፡ ግን ፡ ተክዝ ፡
ሌሎቹ ፡ ሲመኩ ፡ አንተ ፡ ግን ፡ ፍዘዝ ፡
አምረው ፡ ሲያጊያጊጡ ፡ መናኛውን ፡ መልበስ ፡
እንዲሁም ፡ ይሻላል ፡ ሲሣሣቁ ፡ ማልቀስ ፡
ሌላው ፡ ሲጠቃቀም ፡ ሌላው ፡ ሲረዳዳ ፡
ላንተ ፡ ይበጅሃል ፡ ዐውቀህ ፡ ብትጎዳ ፡
ቀኙ ፡ ግራ ፡ ሆኖ ፡ ፍጡር ፡ ሲደናበር ፡
ማለት ፡ ትችላለህ ፡ እኔ ፡ ዐውቄው ፡ ነበር ።
ብርሃንና ፡ ጽልመት ፡ መሬትና ፡ ባሕር ፡
ተራራና ፡ ሜዳ ፡ ጠፈርና ፡ ምድር ፡
ሰዎችና ፡ አራዊት ፡ ጠጠርና ፡ ኮከብ ፡
ውበትና ፡ ጭቃ ፡ ጕድለትና ፡ ጥበብ ፡
አብረው ፡ ተቀላቅለው ፡ ሆነው ፡ ትልቅ ፡ መዓት ፡
ሥራት ፡ የሚያጡበት ፡ የብጥብጥ ፡ ሰዓት ፡
መኖሩን ፡ ካመነ ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ በከንቱ ፡
ሥራት ፡ ልሥራ ፡ ብሎ ፡ ባለም ፡ ላይ ፡ መልፋቱ ፡
ያስደንቃል ፡ በጣም ፡ እወይ ፡ ሞኝነቱ ።
አንድ ፡ አዲስ ፡ ተገኝቶ ፡ ሌላው ፡ ግን ፡ ካረጀ ፡
የሚናደው ፡ ነገር ፡ ላዲሱ ፡ ከበጀ ፡
በዘመን ፡ መለወጥ ፡ እየተነወረ ፡
ይቅር ፡ ከተባለ ፡ ልማድ ፡ የነበረ ፡
ጠቃሚ ፡ ከሆነ ፡ ሲነቀል ፡ ሲጠፋ ፡
ማፍረስም ፡ መሥራት ፡ ነው ፡ ይለናል ፡ ፈላስፋ ።
ዐይን ፡ የለውም ፡ እሉ ፡ የሰነፍ ፡ ልመና ፡
ወደ ፡ አምላክ ፡ ሲጸልይ ፡ ማታ ፡ በልቡና ፡
መንገዱ ፡ ሳይመታኝ ፡ ባቡዋራ ፡ በጭቃ ፡
አድርገኝ ፡ ይለዋል ፡ ላገሬ ፡ እንደበቃ ፡
እንጦጦ ፡ ተኝቼ ፡ አሥመራ ፡ እንድነቃ ።
እየተሻሻለ ፡ እየተለወጠ ፡
አንደኛው ፡ ከሌላው ፡ አምሮ ፡ እየበለጠ ፡
ሁል ፡ ጊዜ ፡ አዲስ ፡ ነገር ፡ ሠርቶ ፡ በመሰብሰብ ፡
በኑሮ ፡ በሥራ ፡ በልማድ ፡ በጥበብ ፡
ካልተፈራረቁ ፡ ለቅሶና ፡ ደስታ ፡
ትካዜና ፡ ዘፈን ፡ ሣቅና ፡ ጨዋታ ፡
ቀይና ፡ አረንጓዴ ፡ ጥቍርና ፡ ብጫ ፡
ኑሮዋችን ፡ ጣዕም ፡ ያጣ ፡ ይሆናል ፡ አልጫ ።
ዓለምን ፡ ካልናቀ ፡ ሰው ፡ መልካም ፡ አይሠራም ፤
ሞቱን ፡ ካላሰበ ፡ አምላኩን ፡ አይፈራም ፡
ሲቀር ፡ እያየነው ፡ ፍጥረት ፡ ሁሉ ፡ ሞቶ ፡
ልባችን ፡ በኀዘን ፡ ይኑር ፡ ተኮራምቶ ፡
ዘወትር ፡ ዕለት ፡ ዕለት ፡ ባንዳንዷ ፡ ደቂቃ ፡
ይህንን ፡ ሊያስታውስ ፡ መንፈሳችን ፡ ይንቃ ፡
ሀብቱም ፡ ሰውነቱም ፡ አፈር ፡ ውስጥ ፡ ሲገቡ ፡
መሬት ፡ የማይበላው ፡ የማይሞት ፡ ጥበቡ ፡
እውነተኛነት ፡ ነው ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ ገንዘቡ ።
የሐሰት ፡ ወገኖች ፡ ተመቸን ፡ እያሉ ፡
ብዙ ፡ ጊዜ ፡ አድመው ፡ እየተማማሉ ፡
እውነትን ፡ ካለም ፡ ላይ ፡ ሊያጠፏት ፡ ተነሡ ፡
እውነት ፡ ግን ፡ ሁል ፡ ጊዜ ፡ መከታ ፡ ለነሱ ፡
ታግላ ፡ እያሸነፈች ፡ ስትኖር ፡ ረግታ ፡
ጠላቶችዋ ፡ ሁሉ ፡ በሱዋ ፡ ጥፋት ፡ ፈንታ ፡
አንድ ፡ ባንድ ፡ ወደቀው ፡ እየተሰበሩ ፡
ከስማቸው ፡ ጋራ ፡ ሁሉም ፡ ጠፍተው ፡ ቀሩ ።
ባለም ፡ ላይ ፡ ተሠርቶ ፡ በብዙ ፡ ጥበብ ፤
ማዕርግ ፡ የሚባለው ፡ የደረጃ ፡ ግንብ ፤
በዚህ ፡ በሚያዳግት ፡ ባቀበት ፡ መንገድ ፡
ግማሹ ፡ ሲወጣ ፡ ግማሹ ፡ ሲወርድ ፡
ከወደ ፡ ዳር ፡ ቆሞ ፡ ማስተዋሉን ፡ ሳይተው ፡
ምንኛ ፡ ደስ ፡ ይላል ፡ ለተመለከተው ።
ብልኅ ፡ አስተዋይ ፡ ሰው ፡ ያለምን ፡ ነገር ፤
ዘልቆና ፡ ጠንቅቆ ፡ የሚመራመር ፡
ትልቅ ፡ ቁም ፡ ነገር ፡ ነው ፡ ረቂቅ ፡ ምስጢር ፡
ብለው ፡ በሹልክታ ፡ አድርገው ፡ ሽፍን ፤
የዚህ ፡ ዓለም ፡ ሰዎች ፡ የሚያወሩትን ፤
በተረዳው ፡ ጊዜ ፡ መርምሮ ፡ እያጣራ ፤
በመገረም ፡ ብዛት ፡ ሥቆም ፡ አያባራ ።
ሰው ፡ ከሚሉት ፡ ከንቱ ፡ የማይለወጥ ፤
ኧረ ፡ ዋጋ ፡ የለው ፡ የማይገለጥ ፤
ምን ፡ ምስጢር ፡ ይኖራል ፡ በዚች ፡ ዓለም ፡ ውስጥ ?
የሥጋና ፡ የነፍስ ፡ የዕድሜንም ፡ ነገር ፤
የመወለድና ፡ የሞትን ፡ ምስጢር ፡
መርምሮ ፡ ሊያስረዳ ፡ ስንት ፡ ሊቅ ፡ ተመኘ ፤
ግን ፡ ሁሉም ፡ በከንቱ ፡ ባሳብ ፡ ባሕር ፡ ዋኘ ፤
ሰው ፡ እንቆቅልሽ ፡ ነው ፡ ፍቺው ፡ ያልተገኘ ።
ደስታ ፡ ጭቃ ፡ ነው ፡ ነፍስን ፡ ያሳድፋል ፤
ተድላ ፡ ጭቅቅት ፡ ነው ፡ ጠባይን ፡ ያጠፋል ፤
እንዶዱ ፡ ኀዘን ፡ ነው ፡ ውሃውም ፡ መከራ ፤
ጠበሉም ፡ ዐሳር ፡ ነው ፡ ነፍስን ፡ የሚያጠራ ።
እጅግ ፡ ደስ ፡ የሚያሰኝ ፡ ነገር ፡ ባየህ ፤ ጊዜ ፤
ደስታህን ፡ ትተህ ፡ ዙር ፡ ወደ ፡ ትካዜ ፤
በዚህ ፡ ደስታ ፡ ውስጥ ፡ ላይን ፡ የተሰወረ ፤
ያንኑ ፡ የሚያህል ፡ በጣም ፡ የመረረ ፤
ሸክሙ ፡ የከበደ ፡ ወዮታው ፡ የጠና ፤
አንድ ፡ ትልቅ ፡ ኀዘን ፡ አይታጣምና ።
ከበደ ሚካኤል የቅኔ አዝመራ አዲስ አበባ · ፲፱፻፶፮ ዓ.ም.