በእጅ ላይ የሚውል የጣት ቀለበት
ባንገት የሚደረግ ወይም በደረት፤
በወርቅ የሰከረ ባልማዝ ልቡ ጠፍቶ፣
ስም የተፃፈበት ሰጭን ለማስታወስ
እጅ የሚዳብሰው የሚቀመጥ በኪስ፤
የሚሰሰትለት የሚሆን ለጌጥ
መንፈስ የሚወደው ሞገስ የሚሰጥ
በጣም የሚደነቅ ሥራው የረቀቀ
ይኸ መታሰቢያ ነው ጠፍቶ ካልወደቀ።
ሲቀመጥ የሚያምር በጠረጴዛ ላይ
ክቡር ድንቅ የሆነ ጧት ማታ የሚታይ፤
ያበባ ማኖሪያ ገፀበረከት
የሚያማምር ኀረግ የተጣለበት
የወዳጅ ስጦታ ወይም ፎቶግራፍ
ለልጅ ልጅ የሚሆን የሚተላለፍ፤
ቤት ካልተቃጠለ ሌባ ካልሰረቀው
ወይ ካልተቀደደ ሕፃን ካልሰበረው
የሩቁን ያቀርባል ይኸ መታሰቢያ ነው።
በደምብ የታሰረ ቀይ ክር ያለበት
በሳጥን የሚኖር የፍቅር ወረቀት፣
"አትርሱኝ" የሆነ የፀጉር ጉንጉን
አስታዋሽ ፈላጊ ጥንት የቀረውን።
ቁልፍ የሚጠብቀው ባመት የሚወጣ
ልብስና መሀረም የሚኖር በሻንጣ፤
ጫማም የውስጥ ልብስ ትኒኒሽ ስጦታ
ለጊዜው ያጠግባል ሲታይ በደስታ፤
ነጋሪ ይሆናል ብል ካላነተበው
ያለፈውን ጊዜ መልሶ ሲያመጣው።
ቁልፍ የማይደብቀው መታሰቢያ ሞልቷል
በግልፅ እየታየ ሊሰወር ይችላል፤
ሳጥን መክፈት የለም ወረቀት ማንበብ
ቦታው ማከማቻው ማደሪያው ነው ልብ፤
ብርሃን አያሻውም ጩለማ አይጋርደው
ጊዜ አይለውጠውም ዓይን እንኳን ባያየው፤
ልስልስ ጣፋጭ ጥፊ ጉንጭ ላይ የሚያርፍ
"እወድሀለሁኝ" ብሎ ሲጋረፍ
የሚያማምረው ጣት ፍፁም አይረሳም
ወረቀት በመፃፍ ዝብዝበ አያሻም።
ወይም አለ ቁጣ ውስጡ የውሸት
ፈገግታን የሚሰጥ ሲያሰላስሉት፤
ወዲያው ተለውጦ ደግሞም በመሳቅ
አፍን ከፈት አርጎ ከንፈርን ለቀቅ፣
ጥርስን አሳይቶ ፈዞ በማስተዋል
ከንፈርን ከከንፈር አምጥቶ በማዋል፤
ሙዚቃው ሲዘፈን ቀዩ ብርሃን በርቶ
ዳንሱን ሲራመዱት በጣም ተጠግቶ፣
ጆሮን ሲማርከው ቀስ ያለው ንግግር
መታሰቢያ ይኸ ነው የማይበላው አፈር፤
ሁኔታው ጊዜውም ቦታው ተጩምሮ
አስታዋሽ በመሆን የሚኖር ነው አብሮ፤
በፍፁም አይዝግም አያረጅ ቢቀመጥ
እያሸበረቀ ጊዜው ሲለዋወጥ፤
ካንጎል አይፋቅም በአእምሮ ተፅፎ
ሲታወስ ይመጣል ብዙ ዘመን አልፎ።
መታሰቢያ ይኸ ነው የተሠራ በጥንት
ሥጋ የመረገው ያጣበቀው ጅማት፤
ቆዳ ያለበሰው በደም የተቀባ
ነፍስና አካል ሆኖ በሰው የሚገባ:
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች መስከረም 1947 – ነሐሴ 1961 · በፈቃደ አዘዘ