የሚሽቀዳደሙት የባሕር ቅርድዶች ወዳሸዋው መጡ
የፀሐዩን ጮራ ይዘው እየሮጡ።
ይርመሰመሳሉ፤፣ ይረበረባሉ
ያብረቀርቃሉ።
ምንድነው ጉዳዩ !
ነፋስ አስቆጥቶ የሚያሯሩጣቸው?
ተልከው ይሆናል አንድ ነገር ይዘው።
ከባሕሩ ማህል ዓሣው ሲነጋገር
ወይም ከሩቅ ጠረፍ መርከብ ሲሽከረከር
ወይም ከጀልባው ሥር።
ማዶ ከሚታየው ከትንሹ ደሴት
ከተንዘራፈጠው ከጋራው አቀበት:
ይዘዋል በመላ።
ማን ያውቃል ምን ይሆን?
ትርጉሙ ረቂቅ ነው የቋንቋቸው መጠን።
እነሱም አያውቁት /ይቻላል ለማለት/
ምን እንዳስነሳቸው አጥመልምሎ ድንገት።
ምን እንደሚሠሩ የት አንደሚሄዱ
የፀሐዩን ጮራ ሲያመጡ ሲወስዱ:
አሸዋ ሲገፉ
ዓሣን ሺከሙ ሲጥሩ ሲለፉ።
ዛጎል አንከባለው ወደዳር ሊያወጡ
ሲጋጡ ሲሮጡ።
አንዱ ሌላ ሲሆን እያበጀ ቅርድድ
ያኛው በመከተል የሱን ቦታ ሲወስድ:
ኑሮአቸው ነው ውሸት
ምሥጢራቸው ባዶ አልቦ ነው ቀለበት
ይኸ ሁሉ ድካም ከቶ ለምንድነው?
መሬት ለማቅናት ነው?
ባሕር ለማስፋት ነው?
አገር ለመያዝ ነው?
ልፋታቸው ከንቱ!
ግን ትርጉም ይሰጣል
ይኸ ነው እውነቱ
ሁኔታው ሲለወጥ የቅርድድነቱ።
ተንደርድሮ መጥቶ ሲሔድ ወዳሸዋው
መሬቱ ሲውጠው።
ወደተነሣበት ዳግም ላይመለስ
ፈርሶ ሲበታተን ከጠረፉ ሲደርስ።
ቅርድዱ የታለ?
የዱሮ ሁኔታው መልኩ ከተጣለ።
ያ ሁሉ መርመስመስ ያ ሁሉ ማብረቅረቅ
ያ ሁሉ መሯሯጥ ያ ሁሉ መፍለቀለቅ
ጠፍቶ ሲዘባረቅ።
መንቀሳቀሳቸው በኋላ ዝም ሲል
ከትንኝ አንስቶ ከቁንጫ ቅማል
ከዝሆን ከግመል።
በጣም አዋቂውን እንስሳ ከሁሉ፥
ሰውን ይመስላሉ።
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች መስከረም 1947 – ነሐሴ 1961 · በፈቃደ አዘዘ