ማለቂያ በሌለው ደማቅ ሰማያዊ፤
ከሩቅ ያለው ጋራ ተነክሮ ሐምራዊ።
በዚያ ላይ ደመናው አንደ ጥጥ ተነድፎ፤
እየተራራቀ ሲያንጃብብ ተቃቅፎ።:
አንተ ነህ መስከረም፤
የሐምሌን ጩለማ የነሐጠሴን ዝናም፣
የሻርከው አንተ ነህ፤
በብርሃን ውበትህ፡
በክረምቱ ወራት ሰማዩን ያስጌጠው፤
የማርያም መቀነት በቀለም ያበደው።
ጤዛው አርሶታል መሬቱ ላይ ለቆ፤
በቀይና ብጫ መስኩ ተለቅልቆ።
ወንዝና ጅረቱ ድንጋይና አፈሩ፤፣
አገሩ ውብ ሆኗል ሜዳው ሸንተረሩ።
ፅንቁጣጣሽ አንተ ስጦታህ የበዛ፤
ለሰው መታሰቢያ ውበት የምትገዛ።
በሸቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፤
ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን።
ከምረው ዘመኑን ካበው ባመት ባመት፤
በወሩ ደረጃ ፍጥረት ይጓዝበት።
ፍየሎች ይዝለሉ ቅጠል ይበጥሱ፤
ከተሰደዱበት ወፎች ይመለሱ።:
ይልቀሙት እህሉን፤ ይሥሩ ቤታቸውን፤
ይስፈሩበት ዛፉን፤
የደስደስ ያሰሙ ንቦች ይራኮቱ፤
ይንጠራሩ አበቦች ይንቁ ይከፈቱ።
አንበሳና ግልገል በመስኩ ይፈንጭጨ፤
ከብቶች ሣሩን ይንጡ፡
ሕፃናት ይሩጡ ይሳቁ ይንጫጡ፤
ዛፎች ይተንፍሱ፤ የነፋሱ ጠረን፤
ይሰራጭ በቦታው ያውደው አገሩን።:
ዓደይ አበባ ነህ የመስቀል ደመራ፤
ጠረንህ አልባብ ነው አየርህ የጠራ።
ያገር ልብስ አንተ ነህ ነጭ እንደበረዶ፤፣
ሰው የሚያጌጥብህ ጥበብህን ወስዶ።
ቡቃያ ነህ እሸት ጓሚያ የበሰለ፤
አረንጓዴ ልብስህ በጌጥ የተሳለ።
ጥቁር አረንጓዴ፤ ብጫማ አረንጓዴ፤
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች መስከረም 1947 – ነሐሴ 1961 · በፈቃደ አዘዘ