ማነህ የተኛኸው?
አእንቅልፍ የደበተህ ሥጋህን ጥለኸው።
ምን ኖረኻል አንተ
ንጊሥ ኖረሀል ወይ፤ ኖረሃል ወይ ጌታ?
ወይ ቁርንጮ ለባሽ ለማኙ ከርታታ?
ሚኒስትር ደጃዝማች ወይም ፊታውራሪ
ባለብዙ ገንዘብ አሽከር አሳዳሪ
ኖረኻል ወይ አንተ?
አጥንትህ ወላልቆ እንዲህ የሻገተ!
ሥራሀ ምን ነበረ? ቤትህ የት ነበረ?
እርስትህ የት ቀረ?
የተመራመረ አዋቂ ፈላስፋ
ብዙ መሰናክል ካለም ላይ የገፋ
ሳትሆን አልቀረህም፣፤
ጉድ ነው! መልክህ የለም።
ማነሽ ማነህ አንተ?
ማናችሁ እናንተ?
ማነሽ በዘመንሽ የውበት እመቤት
ሆነሽ የገዛሽው የወንዶችን ጉልበት?
በክንድሽ ያለቀው
ወጣቱ ጎልማሳ የት ነው የወደቀው?
ምን ኖረሻል አንቺ አጥንትሽ ይናገር?
አንጩት ተሸካሚ
ወይ ኩበት ለቃሚ
ወይ ልብስሽ ያደፈው ጥሬዋ ባላገር፣
ወይም ሽቅርቅሯ እስቲ ተናገሪ?
ሽቱሽ የጎረፈው መንጭቶ ከፓሪ
በወርቅና ባልማዝ በሉል እንደ ሆነ
ተጫውተሽ የሔድሽው ዝናሽ የገነነ።
አስቲ ተናገሪ ቋሚ ያዳምጣል
አንቺ ለመሆንሽ ምስክርሽ የታል?
ያሻኻል ምስክር
ሞተህ ስትቀበር
ድንጋይ ላይ ተፅፎ የሚናገርልህ
ምልክት የሚሰጥ አንተ ለመሆንህ፤
ሐውልት የሚያቆይህ
ዘመድ ያስፈልጋል ከሌላው ለይቶ
መንገደኛ እንዲያውቅህ ቆሞ ተመልክቶ።:
"እገሌ ነው'" ብሎ ታሪክ የሚያወራ
እንዲደነቅልህ ቀሪው ያንተ ሥራ
ተነሥ አንተው ጥራ!
አጎንህ ከተኙት ዓፅሞች በጉድጓድ
አለ ወይ ዘመድህ የምታውቀው ጓድ?
ወዴት ነው አባባ የታለች እማዬ
ጋሼ ወዴት ይሆን የት ቀረች እትዬ?
ጠፍቷል ምልክቱ
አጥንትና ሥጋህ ሲሰነባበቱ።
ከሙታን ማኅበር በመዝገብ ገብተሃል
ማንኛውም አጥንት አስከሬን ሆነኀል።
የሞት ጠባሳ ነህ አስታዋሸ ሥራውን
ከንቱ ነው የምትል አወይ ፍጡር መሆን!
የተንቀረፈፈው እጅ እግሩ ሸምበቆ
የተከፋፈለው ሰረሰሩ ለቆ፤
ጥርሱ ያገጠጠ ዓይኑ የወለቀ
ጎድኑ ተቆጥሮ ጅማቱ ያለቀ፤
የተገጣጠመ የተሠራ ባጥንት
ሥጋ ወዝ የሌለህ የሰው ዘር ምልክት፤
ሆነህ የተኛኸው
የማትታወቀው፤
ምን ኖረኻል አንተ?
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች መስከረም 1947 – ነሐሴ 1961 · በፈቃደ አዘዘ