ጉንጭሽ ፅጌረዳ
ሞቆት የፈነዳ
አይንሽ የጠዋት ጨረር
የበራ ማለዳ።
⁂
የማትጠገቢ የሥንዴ ራስ ዛላ
አገዳ ጥንቅሽ
ጠብ አትይ አንጀቴ ባኝክ ብመጥሽ።
⁂
ቆንጀ ነሽ አንቺዬ
እሳት ነበልባል ነሽ ንዳድ ባከላቴ
ሆነሻል ሙቀቴ
ሆነሻል ህይወቴ።
⁂
የጋለው ትንፋሽሽ
የሞቀው ምላስሽ
ማርኮኝ በከንፈርሽ
እጄን ሰጥቻለሁ
እስረኛ ሆኛለሁ።
⁂
ያንቀጠቅጠኛል ወባ ቅናት ገብቶ
ልቤን አስፈራርቶ
ትኩሳት አምጥቶ።
⁂
ፍቅርሽ አቃጠለኝ በመልክሽ ልተክዝ
እቀፊኝ ልቀዝቅዝ
ንከሺኝ ልደንዝዝ።
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች መስከረም 1947 – ነሐሴ 1961 · በፈቃደ አዘዘ