መልክአ መድኃኔ ዓለም

ለዝክረ ስምከ መድኃኔ ዓለም ሆይ፤ ምስጋና የሁል ጊዜ ተግባራቸው የሆነ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት ተመራምረው ለማይደርሱበት ለስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ። ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤ በሞትህ ሞትን ታጠፋው ዘንድ ከርቤ የተቀላቀለበትን መራራ ሐሞትን ስለኔ ሕይወት የጠጣህ የአቀረብኳትን አነስተኛ የምስጋና መባ በቸርነትህ ተቀበል።

ለስእርተ ርእስከ መድኃኔ ዓለም ሆይ፤ እኛን ስለማዳን መከራን ለመቀበል ዘንበል ላለው ርእስህና ስእርተ ርእስህ ሰላም እላለሁ። ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ከሰማየ ሰማያት ወርደህ ከድንግል ማርያም ተወልደህ በሥጋ ብእሲ በሕፃን አርአያ በተገለጽክበት ወራት። እናታችን ሔዋንን ያሳተ ከይሲ ዲያብሎስ ፈራ ደነገጠ በኅዘንና በልቅሶም ተዋጠ።

ለገጽከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ከሁለቱ ቀራንብቶችህ ጋረ ለሚያንጸባርቀው አመጸኛንና ከዳተኛን በማስደንገጥ ብቻ ለሚገድል ለገጽህ ግርማ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

የኃጢአትን ማዕበል ባሕር እንደምትገሥፀው መጠን። አቤቱ በጋሃነም እሳት ከመቃጠልና ከሲኦል ትላትል ቁንጥጫ በቸርነትህ አድነኝ፤ እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ እንደጋለ ብረትና እንደተሣለ ምሣር ነውና።

ለአዕይንቲከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የቅዱሳንን ጥሪ ለሚሰማ ዕዝንህና ድሆችን ለሚመለከቱ ዓይኖችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በላይ በዘባነ ኪሩቤል ተቀምጠህ የባሕሮችን ጥልቀት ትመለከታለህ። አቤቱ ሰውነቴን ከስይጣን ፈተና ከአመፀኛ ከተንኮለኛ አድናት። አቤቱ ባሕሩን አድርቀህ ደረቁን ሣር የምታለመልም ክሂሎት ያለህ አሸናፊ አምላክ ነህና።

ለመላትሒከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ሕማመ ተጾፍዖን ለመቀበል ለተዘጋጁ ጉንጮችህ ሰላም እላለሁ። ኅሊናን ደስ ለሚያሰኙ አዕናፍህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ ሠራዊተ መላእክት እየተንቀጠቀጡ በፊትህ የሚቆሙ አንተ በቀያፋና ሐና አደባባይ ቆምህ። አቤቱ የኔ ጥፋት በአንተ ዘንድ ተፈላጊ አይደለምና እንደሰማሁትና እንደማውቀውም ሁሉ በመስቀልህ ቤዛነት አድነኝ።

ለአፉከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

አቤቱ እንደከረመ የወይን ጠጅ የሐሞትን መራራነት ለአጣጣመ አፍህና ከናፍርህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ አምላካዊ ተአምራት የማድረግ ሥልጣን በአንተ እጅ የተያዘ በመሆኑ። ዳግም በምትመጣባት በዚያች ዕለት ሑሩ እምኔየ የምትለዋን የፍርድ ውሳኔ እንዳታሰማኝ በቸርነትህ እማፀናለሁ።

ለአስናኒከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ሣለህ አስቀድሞ ሰለዓለም ነፃ መውጣት የሰበከ አንደበትህና መለኮታዊ አስናኖችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ቃልህ የማይታበል የማይለወጥ ነውና መልአከ ሞት ነፍሴን በፊትህ ባቆማት ጊዜ አቤቱ ገጸ ምሕረትህን አትመልስብኝ።

ለቃልከ

መድኃነኔ ዓለም ሆይ፤

አባት ሆይ፤ ይቅር በላቸው በማለት በታላቅ ቃል በመስቀል ላይ ለተናገረ ቃልህ ሰላም እላለሁ። በመስቀል ላይም በሰቀሉህ ጊዜ አንዳችም የተቃውሞ ትንፋሽ ላልትነፈሰ እስትንፋስህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ከዚያ እስከዚህ ድረስ የሠራሁትን ኃጢአቴን ይቅር በል። አቤቱ ቅዱስ ሥጋህን ከበላሁ ክቡር ደምህን ከጠጣሁ በኋላ ነፍሴ ጥፋት እንዳያገኛት በፍጽም ትጋት ደጅ እጠናለሁ።

ለጕርዔከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ክቡር ልዑል ለሚሆን ጕርዔህ ሰላም እላለሁ። በገመድ እየሳቡ ለጐተቱት ክሣድህም ሰልላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀልከው ለሰው ልጅ ደህንነት እንደመሆኑ መጠን ሰለእናትህ ስለ ድንግል ማርያም ብለህ ምሬሃለሁ ይቅር ብየሃለሁ በለኝ። ከአንተ በቀር ቸር ይቅር ባይ የለምና።

ለመታክፍቲከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

በጎለጎታና በቀራንዮ አደባባይ አርዑተ መስቀልን ተሸክመው ለተንገላቱ መተክፍትህ ሰላም እላለሁ። ዙፋኑን በዘባነ ኪሩቤል ለአዘጋጀ ዘባንህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በቀል የሌለብህ አምላክ እንደመሆንህ በቅዱሳኖች በወዳጆችህ አማላጅነት እማፀናለሁ። ስማችሁን የጠራ እምርላችኋለሁ ስትል ቃል ኪዳን ገብትህላቸዋልና።

ለእንግድዓከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የአዳምን ዘር ለማዳንና በጠቅላላው ለዓለም ቤዛ ለመሆን ሐፃውንተ መስቀልን ለታቀፉ ክንድህና ደረትህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ለሰውነቴ መልካሙን የዕረፍት ጊዜ ስጣት። አቤቱ ሰውነቴን፤ ነፍሴን የሚፃረሯት ጠላቶቼ ሁሉ፤ በሲኦል የጨለማን ወለል ላይ ተነጥፈው በእግረ አጋንንት ይረገጡ ይጠቅጠቁ።

ለአእዳዊከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ለቤዛ ዓለም ስትል በፈሰሰው ደምህ፤ ለተነከሩት ለተጠመቁት እጆችህ ሰላም እላለሁ። በሌሊት የሚዘዋወረውን ድንገተኛ ጠላትና በቀን የሚፃረረውን የቀት ኃይል አጋንንት ለሚያዳሽቀው መለኮቱዊ ኵርማህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በጐ ነገርን አስጀምረህ የምታስፈጽም ቸር አምላክ ነህ። አቤቱ ከጐንህ የፈሰሰው ደመ መብረቅ ከላይ ወደታች በተቈለቈለ ጊዜ ድምፀ ጉህናው ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አስተጋባ።

ለኵርናዕከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

በቅዱስ መስቀል ላይ በተሰቀልህ ጊዜ በግራና በቀኝ ተዘርግተው ለተንሰራፉ ክንድህና ወርቾችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣርዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ቤቱ ደዌ መከራ ከሌለበት፤ ተድላ ደስታ ከአለበት ኤዶም ገነት ታገባኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

ለእራኅከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የእናታችን የሔዋንን በደሏን ይቅር ትልላት ዘንድ መከራን ለተቀበሉ መዳፎችህና ዓለማትን ሁሉ በመለኮታዊ ጥበብ ለፈጠሩ ዓሥሩ ጣቶችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

የኃጥአን ነፍስ መጠጊዬ አንተ ነህ እኮን! ለዓለምም የምታበራላት ዕውነተኛ ፀሐይ አንተ ነህ።

ለአጽፋረ እዴከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የዓሠርቱ ቃላተ ኦሪት ትእዛዛት ለተጻፈባቸው ንዑዳት ክቡራት ለሚሆኑ ለእጆችህ አጽፋር ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክረስቶስ ሆይ፤

ክቡር ዳዊት እንደተናገረው ጠላቶቼ ሰውነቱ ዱር ለዱር ትቅበዘበዝ እያሉ እንዳላገጡብኝ በየጊዜው በየሰዓቱ በየዕለቱ ልመናዬን ሳቀርብልህ ፈጥነህ ተቀበለኝ እንጂ ቸል አትበለኝ።

ለገቦከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ኅዘንና ትካዜን ለሚያስወግድ መለኮታዊ ጎንህ ሰላም እላለሁ። በዓለሙ ሁሉ በጭንቅና በመከራ ላይ የሚገኙትንም ለሚያረጋጋ አምላካዊ ከርሥህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

መድረቅ መንጸፍ የሌለበት ባሕረ ምሕረት እንደምሆንህ የቸርነትህን ቃል መቼ ታሰማኝ ይሆን? እያልኩ ሁል ጊዜ አምላኬ አምላኬ እላለሁ።

ለልብከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ናዝራዊ የተባልክ ለአንተ ለእግዚርብሔር፤ ነቢይ ወመንፈሳዊ ለተባልክ ለአንተ ለመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልቡና ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ስለትሕትና ሕፃን ወአረጋዊ እየተባልክ የምትመሰገን አንተን በመስፍኑ በጲላጦስ አደባባይ እንደወንጀለኛ አገልጋይ ባሪያ የሌዊና የይሁዳ ልጆች የሚሆኑ ካህናት እንዴት ሊገርፉህ ተበረታቱ! አቤቱ ለትዕግሥትህ አንክሮ ይገባል።

ለኵልያቲከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

እንደ አጥቢያ ኮክብ በግራ በቀኝ ሆነው ለሚያበሩ ሁለቱ ኵልያቶችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ እግዚአብሔር እየተባልክ ትመለካለህ። አቤቱ አንተ ክርስቶስ ለኃጥአን ስንኳ ሕይወታቸው ነህና፤ አቤቱ ስንልህ በከንቱ እንዳንጠፋ ጠብቀን።

ለኅሊናከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ዳግመኛም ከሰሜን እስከ ደቡብ በዓራቱም ማዕዝነ ዓለም የብርሃኑ ጸዳል ለሚንጸባርቀው ኅሊናህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስትስ ሆይ፤

በዘባነ ኪሩቤል ላይ ዙፋንህን ዘርግተህ የተቀመጥህ አንተ ነህ። የአብን ፈቃድ ትፈጸም ዘንድ ከሰማየ ሰማያት ወደዚህ ዓለም የመጣህ አንተ ነህና ክቡር ምስጉን አምላክ ነህ።

ለአማዑቲከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የኃጥኡን ሰው ውሳጣዊና አፍአዊ ሰውነቱን ለሚቀድሰው ንዑድ ክቡር ለሚሆን ውስጣዊ ገንዝብህና ለአማዑትህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ከዚህ ዓለም ጥፋትና ጥል፡ ጭቅጭቅና ንዝንዝ ሁሉ አድነኝ። በሰማይና በምድር፤ በባሕርና በየብስም ቢሆን ያለአንተ ቸር ሰው ወዳጅ ንጉሥ የለምና።

ለሕንብርትከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

በአምሳለ ቅዱስ መስቀል ማዕተብነ፤ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ለተማተበው ሕንብርትህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ ከችግርና ከፈተና አድነኝ፤ አባትህም በምስሐ ደብረጽዮን በሚያደርገው ታላቅ የምሳ ግብዣ ላይ ይዘኸኝ ግባ ከአንተ በቀር ሌላ የማውቀው ዘመድ የለኝምና።

ለሐቌከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የሲኦልን በር የናሱን መዝጊያ ሰባብረህና ቀጥቅጠህ የብረቱንም ቁልፍ እንደሰም አቅልጠህ ነፍሳትን ከሲኦል በአወጣህበት ሰዓት መለኮታዊ ዝናርን ለታጠቀ ወገብህንና ኃይለአርያምን ለተጐናጸፉ አቍያጾችህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

መሐሪ ይቅር ባይ አንተ እግዚአብሔር እንደመሆንህ መጠን በምሄድበት መንገድ ሁሉ ቀናውን ጎዳና ምራኝ። የጽድቁንና ዕውነተኛውን መንገድ ፈጽሞ ለማውቅ አልችልምና።

ለአብራኪከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ከሁለት እግሮችህ ጋር ወደ ብሔረ ሞት በፈለሱ ጊዜ በደመ ቅንዋት ለተጥለቀለቁ ጉልበቶችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ቃልህ የማይታበል ዕውነተኛ አምላክ ነህ። አቤቱ ጌታዬ እኔን አገልጋይህን ለመጐብኘት በየጊዜው በመመላለስ ወደ እኔ ና! ና! አቤቱ ጌታዬ አንተ የዓለም ግርማ ሞገሱ ነህና።

ለሰኰናከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ፈጻሜ ፍቅር ወሰላም ለሆነው ተረከዝህ ሰላም እላለሁ። ዓለሙን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት የወረድህ አንተ ቸር አምላክ ነህ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

የአርያም ጽንዕ ኃይል ስትሆን እንደደካማ ሰው ክቡዱንና ግዙፉን ዕፀ መስቀል በመሸከም ምንኛ ድካምንና መከራን ልትታገሥ ቻልክ። ለዚህ ረቂቅ ትሕትናህ አንክሮ ይገባል።

ለመከየድከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ያለበደልና ያለአበሳ ሰውና መላእክትን የፈጠርክ ሆይ በብረት ችንካር ለተቸነከሩት ጫማውችህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ ጌታ መሐሪ ይቅር ባይ እግዚአብሔር እንደመሆንህ መጠን በዚያ በቁርጥ የፍርድ ቀን በምትመጣበት ጊዜ ማረኝ ይቅርም በለኝ አቤቱ በፊትህ እንደኔ ያለ በደለኛ የለምና::

ለአጸብዓከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

በለቢሰ ሥጋ ለደከሙና ለወዙ ጣቶችህ ሰላም እላለሁ። በጐዳና ላይ በድንጋይ ዕንቅፋት ላልተሰነካከሉ ለእግሮችህ አጽፋርም ሰላም እላለሁ። ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ፍለጋህ ተመራምሮ ሊገኝ የማይቻል ነው። አቤቱ የወዳጅህ የዳዊት መጽሐፍ እንደ ተናገረው በዚህ ዓለም ስለዕውነትና ስለጽድቅ የደከመ በወዲያኛው ዓለም የዘለዓለም ሕይወት እንዳለው አምናለሁ ተስፋም አደርጋለሁ።

ለቆምከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

አይሁዶች ተሰባስበው በቀራንዮ አደባባይ ለአቆሙት አካለ ቆምህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ግዙፍ ሥጋን በተላበሰ አንደበቴ ልመናዬን ሳቀርብልህ አሳልፈህ ለጠላት አትስጠኝ። እንዳንተ ያለ ጠቃሚ ዘመድ በቂ ወገን አይገኝምና።

ለመልክእከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ለጻድቃን ያይደለ ኃጥአንን ለማዳን በራሱ ደም ራሱ ለተጥለቀለቀ ሥነ መልክእህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በየጊዜው በነጋ በጠባ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ። በመስቀል ላይ ሣለህ አባት ሆይ፤ ይቅር በላቸው በማለት የተናገርከውን የቸርነትና የርኅራኄ ቃል አስቀድሜ ሰምቻለሁና።

ለፀአተ ነፍስከ

በመስቀል ላይ ልዩ ልዩ ልዩ አምላካዊ ተአምራትና ሕማማተ መስቀል ከተፈጸመ በኋላ በገዛ ሥልጣንህ ለተፈጸመው ጸዓተ ነፍስህ ሰላም እላለሁ። ሕሙማንን ለሚፈውስ ልዩ መዓዛ ላለው በድነ ሥጋህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ዓለምን ለማዳን በተሰቀልክበት በዚያን ሰዓት እነሆ ጌታዬ ሆይ፤ ፀሐይ ብርሃኑን ከመሰጠት ተከልክሎ ጊዜው ጨለመ ጨረቃም ደም ሆነ።

ለግንዘተ ሥጋከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ከጽጌረዳ መዓዛ ይልቅ መዓዛ ላለው ግነዘተ ሥጋህ ሰላም እላለሁ። በኢየሩሳሌም አደባባይ ለሚገኘው መካነ መቃብርህም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ሰይጣናዊ በሆነ በይሁዳ ወገኖች ቅናተሞተህ የሔዋን ልጆች ባልተቀበሩበት አዲስ የሚሆን በታነፀ የሕንፃ መቃብር ተቀበርህ። አቤቱ ሞት የማይገባህ ላንተ ምስጋና ይገባል።

ለትንሣኤከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የመቃብር ጠባቂ ጭፍሮችን አሸብሮ የጻድቃንን ትንሣኤ ለገለጠ ትንሣኤህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በልዩ ትንሣኤህ ጨለማን ከአስወገድህ በኋላ በግብር አምላካዊ በዝግ ቤት ገብተህ ደቀመዛሙርትህን በጦር የተወጋውን ጐኔን በችንካር የተቸነከሩትን እጅ እግሬን ተመልከቱ አልካቸው።

ለትንሣኤከ

መድኅኔ ዓለም ሆይ፤

ከእንቅልፍ እንደመንቃት ለሆነ ትንሣኤህ ሰላም እያልኩ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ተአምራትህን እናገራለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ለአዳም ልጆች መድኅን እንደመሆንህ መጠን የእኔን የደካማውን አገልጋይህን ልመና ተቀብለህ አቤቱ ከዚያ ርጉም ከሚሆን ጠላቴ እጅ አድነኝ።

ለዕርገትከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

በዓውሎ ነፋስና በእሳት ነበልባል አምሳል መንፈስ ቅዱስን ትልክልን ዘንድ በነጐድጓድና በመባርቅት የሠረገላ ዘባን ለተከናወነ ዕርገትህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

በአንዲት መንግሥትህ መንግሥቱ ለዘለዓለም አገዛዙም ለትውልደ ትውልድ ነው እያሉ ሰማያውያን መላእክት በየዕለቱ በየሰዓቱ ያመሰግኑሃል።

ለዕርገትከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

የቃል ኪዳን ሥነ ሥራዓት ለፈጸመ ዕርገትህና ሁሉን ለማዘጋጀት በኋለኛው ዘመን አመጣጥህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ቅድመ ዓለም በጌትነቱ ክብር ከአባትህ ዘንድ የነበረ ወደዚህ ዓለም በዓውሎ ነፋስ አምሳለ የላክኽው እሱ መንፈስ ቅዱስ የኃጢአቴን እሾህ በማቃጠል አቤቱ እሱ ኃይሉን ይግለጽ።

አልቦ እምሰብእ

ከሰው ወገን ማንም እንደኔ ኃጢአት የሠራ በደለኛ የለም። እንደ አንተም ያለ መሐሪ ይቅር ባይ አምላክ አይኖርም።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ዓለማትን ሁሉ የፈጠርህ ፈጣሪ እንደመሆንህ መጠን በኋለኛው ዘመን በዓለም ላይ ለመፍረድ በምትመጣበት ጊዜ ከጐንህ በፈሰሰው ደም ኃጢአቴን እጠብልኝ አሜን።

አቄርበ ወትረ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤፡

ስለኃጢአቴ ሥርየት በጭንቅና በመከራ ምስጋናህን ዘወትር አቀርባለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

የሰማይንና የምድር ጌታ እንደመሆንህ እኔ ጐስቋላው አገልጋይህ ኃጢአቴን ይቅር ብለህ ማደሪያዬን ስጠኝ እያልኩ በምለምንህ ጊዜ በዱርም ቢሆን በተራራ ላይ በአስፈላጊው ቦታ ሁሉ በፍላጎቴ መጠን ምግቤን አዘጋጅልኝ።

አጽምዓኒ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

መሪር የሆነ የሰቆቃው ነገር የምጽፍልህ ነኝና በጆሮህ አድምጠህ ቅዱሳን በሆኑ እጆችህ ጽሑፌን ተቀበለኝ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

መላእክት ሊቃነ መላእክት በመንቀጥቀጥ በፊትህ የሚቆሙ አንተ በጲላጦስ አደባባይ ቆምክ እኮን! አቤቱ። ዬ ዬ ዬ ስለኛ ጎንህን እንደዚህ ዓለም ሰው ተቈጠርክ እኮን! አቤቱ። ዬ ዬ ዬ አንተ አምላክ ስትሆን ስለእኛ ጐንህን በጦር ተወጋህ አቤቱ!።

ኦ ሊቀ ካህናት

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

አቤቱ የካህናት አለቃ ስትሆን እንደቀማኛ እንደ አመፀኛ እንደ ወንጀለኛ የራሄልና የልያ ልጆች የኋሊት አሠሩህ። እኮን! አቤቱ!።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ስለኛ ለሞት ተላልፈህ ተሰጠህ እኮን! አቤቱ! ዬ ዬ ዬ ስለኛ በጦር ወጉህ። አቤቱ! ዬ ዬ ዬ ንጽሕ ክቡር ሥጋህን መሬት ሸፈነው። አቤቱ!።

ክርስቶስ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ኃያላን ሊቃን መላእክት በፊትህ መቆም የማይቻላቸው። አንተን ልባቸው እንደ ድንጋይ የጠጠረ ጭፍሮች በሕዝብ አደባባይ ፊት አቆሙህ አቤቱ!!

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ያለመጉደል እግዚአብሔር ዘሲና እግዚአብሔር ዘግብፅ እየተባልክ የምትመሰገን አንድ እግዚአብሔር ነህ። ዬ ዬ ዬ ስለኛ በእንጨት ላይ ሰቀሉህ አቤቱ! ዬ ዬ ዬ አዲስ በታነፀ መቃብር ጨምረው ቀበሩህ። አቤቱ!

ተማኅፀንኩ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

መጻጻውን መሪር ሐሞት በአጠጡህ ጊዜ ሁሉ ተፈጸመ በማለት በ9 ሰዓት በገዛ ሥልጣንህ ነፍስህን ከሥጋህ ለለየህባት ፀዓተ ነፍስህ ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

የኃያላን ጌታ የፍጥረታትም ሁሉ ፈጣሪ እንደ መሆንህ በዚያች ነፍስህ ከሥጋህ በተለየበት ሰዓት የሲኦል ጠባቂዋ እስኪፈራ ሞት እስኪደነግጥ ድርስ መሬት ተነዋወጠች መቃብራት ተከፋፈቱ።

ተዘከረነ እግዚኦ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

አስቀድሞ ፈያታዊ ዘየማንን እንዳሰብከው አቤቱ አዳኝ ቤዛ በሚሆን መስቀልህ አስበን።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ ቸር ጠባቂ ነህና እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ። አቤቱ እኔን መከረኛውን ኅዘነተኛውን ሰው በምስጋናህ የወይን ጠጅ አስደስተኝ አረጋጋኝ።

ኦ ዘአዖሩከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

እጅ እግርህን በመቸንከር የኛን መከራ አቸክመው በቀራንዮ ተራራ ላይ ለአቆሙህ ማቆም ሰላም እላለሁ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለሀ የአብ የባሕርይ ልጁ ሆይ በአንተ መከራ ጽኑ ከሆነ ከመከራ ሥጋና ከዳግመኛ ሞት እኔን አገልጋይህን አድነኝ::

ምንተ ይዜኑ ፡፡

መድኃኔ ዓለም ሆይ ፤

አቤቱ የሞትህን ዜና በዓይኑ የተመለከተ በጆሮውም የሰማ ሰው እሱ ምን ዓይነት ነገር ሊናገር ክሂሎት ይኖረዋል ።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

አቤቱ ተመልከ ጼዴቅ ምሳሌው ካህን ሆይ አንተ ግን በአንደበቱ መናገር ሲጀምር ባርከው አክብረው በሱም ላይ ቅዱስ መንፈስህን አሳድር።

ዘጸውአ ስመከ

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ስምህን የጠራ መታሰቢያህንም ያደረገ እሱ በዚያ በቁጥር የፍርድ ቀን ከንቱ ሆኖ አይቀርም።

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ቅድመ ዓለም የነበርክ ዛሬም ያለህ ለዘለዓለሙም ጸንተህ የምትኖር አምላክ ስትሆን የታሠሩ አገልጋዮችህን አንተ ታሥረህ ፈታሃቸው በሞትህም ሞተህም የሞቱትን ወገኖችህን አስነሣሃቸው።

ለኅጡአ ምግባር

መድኃኔ ዓለም ሆይ፤

ሃይማኖት ስንኳ ቢኖረኝ በጎ ምግባር የሌለኝ አነስተኛው አገልጋይ ማደርያ ቤት መኖሪይ ቦታዬ ከቅዱሳኖችህ ጋር ይሆን ዘንድ ፈቃድህ ይሁን አቤቱ!

ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤

ከከንቱ ሞት አድነኝ። ሁሉ ከንቱ ነው። የዚህ ዓለም ንብረት የከንቱ ከንቱ ነው። ሁሉም ኃላፊ ጠፊ ነውና።

ስብሐት ለከ

አቤቱ በፍጥረቱ ሁሉ አንደበት የምትመሰገን ለአንተ ለመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይገባል። አቤቱ ለተራቆቱት ልብስ የምትሆናቸው ለአንተ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይገባል።

አቤቱ ነፍስና ሥጋን አዋህደህ በምግባር ሃይማኖት አጽንተህ የምታከብራቸው ለአንተ ለመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይገባል።

አቤቱ በመንግሥትህ ሽረት በህልውናህ ሞት ኅልፈት የሌለብህ ለአንተ ለንጉሥ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይገባል አቤቱ የቅዱስ አብ አካላዊ ቃል ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንተ ክብር ምስጋና ይገባል ለዘላለሙ አሜን።

Source: awdemehret.org

← መጽሐፍ