ውዳሴ አምላክ አማርኛ

ከቁጣ የራቅህ ይቅርታህ የበዛ ጻድቅ ልበ ሰፊ መሐሪ ሆይ አከብርሃለሁ። ዕለት ዕለት ስበድል ታግሠህ ጠብቀኸኛልና፤ ንስሐ እንገባ ዘንድም ለሁላችን ሥልጣን ሰጠኸን፤ስለዚህ እናከብርህ ዘንድ ክቡር ስምህን እናመሰግን ዘንድ ታገስኸን ስለምትሠራው ሁሉ የፍጥረት ሹም ሆይ ኀዘንና ፍርሃትን ድካምንም የምታመጣበት ጊዜ አለና። በነቢያት የዘለፍክበት ጊዜም ነበርና ኋላ ግን በአንድ ልጅህ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መታየት ጐበኘኸን። ካለመኖር ወደ መኖር የፈጠርኸን አንተ ነህ አባታችንም ጌታችንም አንተ ነህ። ችጋረኛ የምሆን እኔስ ከፊትህ ልናገር አይገባኝም ከኃጥአን የምበልጥ ኃጥእ ነኝና። ክብርት ሕግህንም ያረከስኩ ነኝና ከኃጢአቴ ትዕግሥትህን ስለ አበዛህልኝ አመስግንሃለሁ። በፈቃድህ ቸል ብለህ እስከ አሁን ያለ ፍርድ ጠበቅኸኝ። እኔ ግን ስለ በደሌ ለፍርድ የተገባሁ ነኝ ስለ ኃጢአቴም ለስቃይና ከፊትህ ለመውደቅ፤ ነገር ግን ሰውን ስለመውደድህና ስለ ትዕግሥትህ እስከ አሁን ጠበቅኸኝ። መሐሪ ጌታ ሆይ፤ ስለዚህ አመሰግንሃለሁ መጠን ለሌላት ትዕግሥትህና ለጌትነትህ የሚገባ ምስጋናን አመሰግንህ ዘንድ ሥልጣን የሌለኝ የተናቅሁ ጎስቋላም ብሆን የእኔን የባሪያህን ጎስቋላና ደካማ ልመናዬን ስማኝ። ወሰን በሌላት በፍቅርህ ብዛት እስከ ዘለዓለሙ ክብርና ምስጋና መገዛትም ለአንተ ይገባል አሜን በእውነት። ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕቀብ ሕይወትየ ወሥረይ ኃጢአትየ ሊተ ለ....።

ማር ይስሐቅ ፪ኛ ምዕራፍ

ወንድሜ ሰውነትህን ዘወትር ዝለፋት ከሥጋ የምትለዪበት የምታልፊበት ጊዜ ደርሷል በላት። ባለሽበት ኋላ ጥለሽው በምትሄጂ ሥራ ዛሬ ለምን ደስ ይልሻል? እርሱን በማየት ጥቂት ዘመን ተድላ ደስታ የምታደርጊበት ኋላ ብዙ ዘመን በምታጭው የቀደመ ሥራሽን እወቂ የሠራሽው ሥራ ምንም እንደሆነ አስቢ፤ጽድቅም እንደሆነ ኃጢአትም እንደሆነ፤ ያለ ዘመንሽን ከማን ጋር ፈጸምሽው? ከጌታ ጋር ነው? ወይስ ከሰይጣን ጋር ነው? ደክመሽ የሠራሽውን የሚቀበልሽ ማን ነው? ጌታ ነው? ወይስ ሰይጣን ነው? በትሩፋትሽ ማንን ደስ አሰኘሽ? ጌታን ነው ወይስ ሰይጣንን ነው? በጊዜ ሞትሽ ሊዋሐድሽ የሚመጣው ማን ነው? በመንግሥተ ሰማይ ዐርፈሽ ትኖሪ ዘንድ በሥራሽ ደስ ያለው ማን ነው? ለማን ብለሽ ደከምሽ? ለማን ብለሽ መከራ ተቀበልሽ? ለመንግሥተ ሰማይ ብለሽ ነውን? ደስ ብሎሽ ታገኚው ዘንድ አኳኋኑስ ምንድነው? ነፍስሽ ከሥጋሽ በተለየች ጊዜ በመንግሥተ ሰማይ ይዋሐድሽ ዘንድ ገንዘብ ያደረግሽው ምንድነው ምን ምግባር ነው? በማናቸው እርሻ ሊያውሉሽ ተቃጠሩሽ በማናቸውስ መዓርግ ተቃጠሩሽ? በባለሠላሳ ነው? በባለስልሳ ነው? ወይስ በባለመቶ ነው? ነፍስሽ ከሥጋሽ በምትለይበት ፀሐይ ዕድሜሽ በገባ ጊዜ ዋጋሽን እሰጥሻለሁ ያለሽ ማነው? ጌታ ነው? ወይስ ዲያብሎስ ነው? ነፍሴ ሆይ ሰውነትሽን መርምሪ ዕዳሽ በማናቸው ቦታ እንደሆነ እወቂ፤ መንግሥተ ሰማይም እንደሆነ ገሃነምም እነደሆነ እወቂ ለሚያርሱ ሰዎች አሞጭ እሬት የሚያፈራ እርሻሽን ያረስሽ ብትሆኝ ማለት በሚሠሩት ሰዎች ፍዳን የሚያመጣ ኃጢአትን ብትሠሪ እያዘንሽ እየተቆረቆርሽ አልቅሽ ለምኝ። ከቍርባን ከመሥዋዕት ይልቅ በሱ ምክንያት ወዶ በሰው በሚያድርበት ገንዘብ ያድርበት ዘንድ ክቡራን መላእክት ደስ በሚላቸው ደስ ይላቸው ዘንድ አንደበትሽ እየራራ ያመስግን። ግራ ቀኝ ፊትሽን በዕንባ እጠቢው መንፈስ ቅዱስ ያድርብሽ ዘንድ ከኃጢአትሽ ይለይሽ ያነጻሽ ዘንድ መጥቶ ያድርብሽ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያለቀስሽ ለምኚልኝ የልቅሶ ዜማ ማርያምን ማርታን ጥሪያቸው ማለት አብነት አድሪጊያቸው የልቅሶ ባለቤቶች ናቸውና። ለአልዓዛር ብሎ ወደ አለቀሰ ወደ ጌታ ያዝንልሽ ዘንድ ለምኝ ራርቶ ብዙ ልቅሶን ወደሚሰጥ ጌታ ለምኝ። ምርር ብዬ ያለቀስሁት ዕንባዬን ተቀበልልኝ እያልሽ ወደ እርሱ አልቅሽ። በመልዕልተ መስቀል በተቀበልከው መከራ ከደዌ ኃጢአት አድነኝ። በመስቀል ላይ በቆሰልከው ቍስል ከቍስለ ኃጢአቴ አድነኝ ከመከራ አድነኝ። ደሜን በደምህ አንጻው ብለሽ ለምኝ። ከፍዳ ከኃጢአት የሚያድን ደምህን ከሥጋዬ ጋር አዋሕድልኝ። በመስቀል ላይ በጠጣኸው ሐሞት፤ ሰይጣን እሷን ከሚያሠራት ኃጢአት ለይተህ በሰውነቴ ጣዕም አሳድርባት። በመስቀል ላይ የተዘረጋ ሥጋህ፤ አጋንንት በምክራቸው ወደ ገሃነም ለማውረድ የሳቡት ልቡናዬን ወደ አንተ ይስቀለው ወደ ፈያታይ ዘየማን ዘንበል ባለ እራስህ አጋንንት በብረት ኃጢአት የመቱት ራሴን ከፍ ከፍ አድርገው። «እምከመ ተለዓልኩ እምድር እስሕብ ኵሎ ኀቤየ» ብለህ በማይታበል ቃልህ እንደተናገርክ። ዮሐ.፲፪፥፴፪ በመስቀል የተቸነከሩ እጆችህ ከኃጢአት ከፍ ከፍ ያድርጉኝ ርኩሳን አይሁድ ትፍ ያሉበት የጸፉት ፊትህ ኃጢአት ሠርቶ ያደፈ ሰውነቴን ፊቴን ይጠበው። በመስቀል ተሰቅለህ ሳለህ «አባ አመኃፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ» ሉቃ.፳፫፥፵፮ ብለህ የለየሃት ነፍስህ በቸርነትህ መርታ አንተ ወደ አለህበት ታድርሰኝ። «ምነው አታዝንም?» ትለኝ እንደሆነ አንተን ለመሻት ያዘነ ልቡና የለኝምና። «ምነው ንስሓ አትገባም?» ትለኝ እንደሆነ፤ ጻድቃን ወደ ማታልፍ ርስታቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት ተመርተው የሚደርሱበት ንስሓ ኀዘን የለኝም፤ እሊያ ንስሓ ገብተው የሠሩትን ሥራ አልሠራሁምና። ጌታዬ ሆይ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ እንባ የለኝም የዚህን ዓለም ሥራ በማሰብ ልቦናዬ ደከመ፤ተቆርቁሮ ወደ አንተ ያለቅስ ዘንድ አይቻለውም እነሆ በኃጢአት ብዛት ልቡናዬ ተባረደ። አንተን ወዶ በሚያፈሰው እንባ ፍቅር መቃጠል አይቻለውም። የሀብታት የምስጢራት መገኛ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ግን ራርተህ ፈጽሞ መመለስን ስጠኝ። በፍጹም ልቡናዬ አንተን ለመሻት እወጣ ዘንድ ያዘነ ልቡናን ስጠኝ። ከአንተ በመራቅ ከአንተ በመለየት ተሰጥቶኝ የነበረውን ክብር አጣዋለሁ። ቸር ንጉሥ ሆይ ዛሬ ግን በለጋስነትህ ስጠኝ።

ዘመን የሌለው ልደትን አካልን ዘእምአካል፣ባሕርይን ዘእምባሕርይ የወለደ አባትህ አንተን መምሰልን ያጸናብኝ፤ ያሳድርብኝ ዘንድ ከክብርህ ወገን ስጠኝ ካልኩህ አንተ ግን አትጣለኝ። ከከበረ ሕግህ ወጣሁ ከፊትህ ተለየሁ። አንተም እኔን ለመፈለግ ውጣ። «እንደገባ ይውጣ እንደወጣ ይቅር» አትበለኝ። ምእመናን ወደ አሉበት ወደ መንግሥተ ሰማይ አግባኝ። ከመንጋ በጎች ከተመረጡ ከጻድቃን ጋር እንድቆጠር አድርገኝ። ንጹሕ ልቡናን ላግኛት የሚል ንጹሕ ልብ የሚረዳት የአምላክነትህ ገንዘብ የምትሆን እህል ምስጢርህን መግበኝ ከአንተ የተገኘውን ምስጢር የማይበት በአንተ ስለአመኑ ስለሚጨነቁ የሚሰጥ ጸጋ ክብር ነው የጭንቅ ጭንቅ የሚሆን መከራውን ለሚታገሡ ልዩ ልዩ የሚሆን ሥቃይን ለሚታገሡ ሰዎች የሚሰጥ ክብር ለሁላችን ምስጢር የሚገለጽበት ክብሩን በቅተን እናገኘው ዘንድ ጸጋውን የበቃን ሆነን ያገኘን ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ሰውን በመውደዱ ዛሬ በአለው ዓለም በሚመጣውም ዓለም፤በማይፈጸመው ዓለም ሰውን በመውደዱ አሜን በእውነት። ኦ እግዚእየ ወአምላኪየ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት መገኛ መዓትህ የራቀ ትዕግሥትህ የቀረበ ቸርነትህ የበዛ ዕቀብ ሕይወትየ ወሥረይ ኃጢአትየ ሊተ ለ.......።

ጸሎተ ምናሴ ፩፥፩-፲፫

አቤቱ ዓለምን ሁሉ የምትገዛ የአባቶቻችን አምላካቸው። የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም የጻድቃን የዘራቸውም ሁሉ። ሰማይና ምድርን ከዓለሞቻቸውም ሁሉ ጋር የሠራህ። ባሕርን በቃልህ ትእዛዝ የገሠጽሃት፤ጥልቆችን የዘረጋህ የሚያስፈራውንም ያተምህ ይኸውም በምስጉን ስምህ ነው። ሁሉ ከኃይልህ ፊት የሚናወጽና የሚንቀጠቀጥ ሆይ ለምስጋናህ ከፍታ ዳርቻ የለውምና የቍጣህ መቅሠፍት በኃጥአን ላይ የሚያስፈራ ነው። ለትእዛዝህ ይቅርታ ስፍር ቍጥር የለውም፤ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ብቻህን ከፍ ያልህ ነህና። ከቍጣ የራቅህ ይቅርታህም የበዛ መሓሪ ነህና። በሰው ልጆች በደል ላይም የምትመለስ ነህ። አሁንም የጻድቃን አምላክ ሆይ ንስሓን የሠራኸው ለጻድቅ አይደለምና አንተን ላልበደሉ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም አይደለምና፤ ወደ እኔ ወደ ኃጢአተኛው ንስሐ ተመለስ እንጂ። ከባሕር አሸዋ ቁጥር ይልቅ በድያለሁና። ኃጢአቴም ብዙ ነውና፤ ከበደሌም ብዛት የተነሣ የሰማይን ከፍታ አይ ዘንድ ላንጋጥጥ አግባቤ አይደለም። በእግር ብረት ደከምኩ ነፍሴን ከኃጢአቴ አሳርፋት ዘንድ በዚሁም አላረፍሁም፤ ቍጣህን አነሣሥቻለሁና፤ ክፉውንም በፊትህ ሠርቻለሁና ክፉውንም ስጠብቅ የማይረባኝንም ሳበዛ። አሁንም በልቡናዬ ጉልበት እሰግዳለሁ፤ የአንተን ምህረት እየለመንኩ አቤቱ ጌታዬን በደልኩ ኃጢአቴንም እታመናለሁ። እማለላለሁ እለምንህማለሁ። ይቅር በለኝ አቤቱ ይቅር በለኝ። ለኃጢአቴም አሳልፈህ አትስጠኝ። ለዘላለምም ክፋቴን አትጠባበቀኝ፤በምድርም ጥልቅ ውስጥ አትበቀለኝ፤ አቤቱ አንተ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች አምላክ ሆይ፤ ቸርነትህ በእኔ ላይ ይገለጽ ዘንድ አግባቤ ሳይሆን በቸርነትህ ብዛት አዳንከኝ። በሕይወቴ ዘመን ሁሉና በጊዜው ሁሉ አመሰግንሃለሁ። የሰማዮች ሠራዊት ሁሉ አንተን ያመሰግናሉ። ለዘላለምም ምስጋና ለአንተ ይገባል አሜን በእውነት።

Source: awdemehret.org

← መጽሐፍ