ውዳሴ ማርያም አማርኛ

በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ መስቀል ፊቴን እና መላ ሰውነቴን ሦስት ጊዜ አማትባለሁ። በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን(፫ ጊዜ ማማተብ)

፩፤ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ንጹሕ ልዩ ክቡር ጽሩይ በሆኑ በሦስትነት ወይም በሥላሴ እያመንኩና እየተማፀንኩ ጠላቴ ሰይጣንን እክድሃለሁ። በእዚች በእናቴ በቤተ ክርስቲያን ፊት ቆሜ እክድሃለሁ። ለዚህም ምስክሬ ማርያም ናት በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም እሷን አምባ መጠጊያ አድርጌ እክድሃለሁ።

፪፤ አቤቱ እናመሰግንሃለን ፤ አቤቱ እናከብርሃለን ፤ አቤቱ እንገዛልሃለን ፤ አቤቱ ቅዱስ ስምህን እናመስግናለን ፤ ጉልበት ሁሉ የሚሰግድልህ ፤ አቤቱ እንሰግድልሃለን ፤ አንደበትም ሁሉ ላንተ ይገዛል ፤ የአምላኮች አምላክ ፤ የጌቶች ጌታ ፥ የንጉሦችም ንጉሥ አንተ ነህ። የሥጋም የነፍስም ፈጣሪ አንተ ነህ። እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ቅዱስ ልጅህ እንዳስተማረን እንጠራሃለን።

አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግስትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን።የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ በደላችንንም ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል። አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ መንግስት የአንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ፤ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን በሃሳብሽ ድንግል ነሽ፣ በሥጋሽም ድንግል ነሽ። የአሸናፊው የእግዚአብሔር እናት ሆይ፤ ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል። ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽና የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ ልዑል እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ከተወደደው ልጅሽ ከጌታችን መድኃኒትችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታን እና ምሕረትን ለምኝልን ኃጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ለዘለዓለሙ አሜን።

የሃይማኖተ ጸሎት

ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ሰማይና ምድርን የፈጠረ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ሳይፈጠር ከርሱ ጋር በነበረ አንድ የአብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባሕርዩ ከአብ ጋር የሚስተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ በሰማይም ካለው በምድርም ካለው ያለርሱ ምንም ምን የሆነ የለም ስለኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ ፣ ደግሞ ስለኛ ተሰቀለ በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን እርሱ መከራን ተቀበለ ሞተ ፣ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፣ በቅዱሳት መጻህፍት እንደተጻፈ በክብር በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ። በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፣ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ በምስጋና ይመጣል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም። በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን እርሱ ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረፀ ከአብ እና ከወልድ ጋራ በአንድነት እንሰግድለታለን ፣ እናመሰግነዋለን እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረው ነው ከሁሉም በላይ ብምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት (በሠሯት) በአንዲት ክብርት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን።

አሸናፊ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ ትመሰገናለህ። ምስጋናህም በሰማይ በምድር የመላ ነው። ክርስቶስ ላንተ እንሰግድልሃለን ከሰማያዊ ከቸር አባትህ ጋራ አዳኝ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ እንሰግድልሃለን ወደዚህ ዓለም መጥተህ አድነኸናልና።

ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደት እሰግዳለሁ (3 ጊዜ በል) ። አንድ ሲሆን ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ለሚሆኑ እሰግዳለሁ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም እሰግዳለሁ፣ ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀልም እስገዳለሁ። መስቀል ኃይላችን ነው ፣ ኃይላችን መስቀል ነው ፣ የሚያፀናን መስቀል ነው ፣ መስቀል ቤዛችን ነው ፣ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን ያመነውም እኛ በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።

ለአብ ምስጋና ይገባል፣ ለወልድም ምስጋና ይገባል፣ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል (3 ጊዜ በል)። አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል። ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ምስጋና ይገባል። ክርስቶስ በቸርነቱ ያስበን ዘንድ ዳግመኛም ፣ በመጣ ጊዜ እንዳያዳፍረን ፣ ስሙን ለማመስገን ያነቃን ዘንድ ፣ እርሱንም በማምለክ ያጸናን ዘንድ፣ እመቤታችን ጸሎታችንን አሳርጊልን ፣ ኃጢአታችንንም አስተሥርዩልን በጌታችን መንበር ፊት ጸሎታችንን አሳርጊልን ፣ ይህንን ኅብስት ላበላን ይህንንም ጽዋ ላጠጣን ምግባችንን እና ልብሳችንን ላዘጋጀልን ኃጢአታችንንም ሁሉ ለታገሠልን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለሰጠን እስከዚችም ሰዓት ላደረሰን ለእሱ ለልዑል እግዚአብሔር ፍፁም ምስጋና ይገባዋል ለወለደችውም ለድንግልም ምስጋና ይገባል። ለኢየሱስ ክርስቶስም መስቀልም ምስጋና ይገባል። የእግዚአብሔር ስሙ ፈጽሞ ይመሰገን ዘንድ ዘወትር በየጊዜያቱ እና በየሰዓቱ ምስጋና ይገባል።

እናታችን ማርያም ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን እያልን እንሰግድልሻለን እንማልድሻለን ከአዳኝ አውሬ ታድኝን ዘንድ ተማጽነንብሻል ስለ እናትሽ ስለ ሐና ብለሽ ስለ አባትሽ ስለ ኢያቄም ብለሽ ድንግል ማኅበራችንን ዛሬ ባርኪልን።

አምላክን በድንግልና የወለደች የእመቤታችን የማርያም ጸሎት ምርያምም አለች ነፍሴ እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል። የባሪያይቱን መዋረድ አይቷልና። እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል። እርሱ ብርቱ የሚሆን ታላቅ ሥራን ለእኔ አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው። ለሚፈሩትም ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ነው ኃይልን በክንዱ አደረገ። በልባቸው አሳብ የሚኮሩ ትዕቢተኞችን በታተናቸው ብርቱዎችንም ከዙፋናቸው አዋረዳቸው የተዋረዱትንም ከፍ ከፍ አደረጋቸው የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው ምሕረቱን እንዲያስብ እስራኤል ባሪያውን ተቀበለ። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩም እስከዘለዓለሙ ድረስ እንደተናገረው።

Source: awdemehret.org

← መጽሐፍ