ድንቅ ነው

ድንቅ ነው ልዩ ነው ልዑል የእኛ ጌታ
ምስጋና ይድረሰው ከጠዋት እስከ ማታ
የማይመረመር በሰው ልጅ ሕሊና
ረቂቀ ባህርይ ገናና ነውና
ያለ የነበረ ከዘመናት በፊት
ለዘለዓለም ኗሪ ፈጣሬ ዓለማት
በፍጥረታት ሁሉ የሚመሰገነው
ኃያሉ ጌታችን በእውነት ግሩም ነው
በፍጹም ልዩ ነው የእርሱ ጌትነቱ
አልፋና ዖሜጋ ጽኑ ነው መንግሥቱ
በመላእክት ዓለም በሰማይ ከተማ
ለክብሩ ሲዘመር ማኅሌት ሲሰማ
ያለ ምንም እረፍት በቀንና ሌሊት
ንጹሐን መላእክት የሚያመሰግኑት
አዳምን ለማዳን ፍጹም በመውደዱ
የማይሞተው አምላክ ሞተ በፈቃዱ
ምሥጢሩ ረቂቅ ነው ለሰዎች አእምሮ
ፍቅሩ ያስደንቃል ስናየው በአንክሮ
← መዝሙር