” የአይን ፍቅር የራብ አድማ የሚያስመታ ሆኖ ነው አሁን? ጥጋብ ነው እንጅ:: ” ሲል ተቀደደ። ድንግጥ አልኩ ።
ከ ወጉ የተወሰደ
ሰሞኑን አድማ እንደመታሁ የሰማ ሁሉ የየራሱን ሀሳብ መስጠት ይዟል ።
ሐሳብ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ቅደመ ስነስርዓቶች ቢቀመጡ ኖሮ እኔ ብቻ ነበርኩ አስተያየት ሰጪ ሆኜ የምገኘው ። ብቻ ይሉኝታውን ያጣ ሁሉ አስተያየቱን በአድማዬ ላይ ለክቦብኝ ያልፍ ይዟል ።
” ምን እባክህ…. ” ሲል ሰማሁት (ቀልቤ የማይወደው ከላባ ብጤ ነው) በሱ ቤት እሱ አይቶኛል እኔ አላይቸውም …
ሲያወራ ድምፁን መመጠን አይችልም ፣ ከጎኑ ላለው ጓደኛ ሳይሆን ከወንዝ ማዶ ላለ ሰው የሚያወራ ነው የሚመስለው ..
ብቻ የሆነ ሶሻል ሚዳያ ድምሰሳ ላይ የነበርሁ ቢሆንም ገታ አድርጌ መስማት ያዝሁ ።
” ምን ባክህ በርግጥ አድማ በእሱ አልተጀመረም .. ስንቶች ናቸው መንግስትን ተቃውመው የራብ አድማ የመቱት?.. ሰምተህ አታውቅም ? በዚያ ላይ ምክንያቱ በቂ አይደለም .. “
ከጓደኛው ‘እንዴት ?’ የሚል መልስ ቢጠብቅም አልተሳካም ። እራቁ ብዬ ስሰጋ ትንንሽም ቢሆን እንድሰማቸው በሚያስቸል ርቀት ሁለት ሰው ማስቀመጥ በምትችል የድንጋይ ወንበር ተቀመጡ !
” የአይን ፍቅር የራብ አድማ የሚያስመታ ሆኖ ነው አሁን? ጥጋብ ነው እንጅ:: ” ሲል ተቀደደ።
ድንግጥ አልኩ ።

“tiktok” አካውንቴን እያጠፋሁ የነበረ ቢሆንም፤ ለመደምሰሻ የሚሆን በቂ connection እና ትዕግሥት አልነበረኝም ።
የአይን ፍቅር ነው አሉ ደሞ? አልሁ ለራሴ ለማልቀስ እና ለመቦከስ የተመቸ ስሜት ውስጥ ስደነቦቅ እየተሰማኝ።
ያንን ትልቅ ውሸት ከዋሸ በኋላ ከጓደኛው ምንም ምላሽ ባለማግኘቱ ቀጠለ…..
” አድማ መቀለጃ ይሁን ? የማንም ጥርቅም …. “
መታጋስ አልቻልኩም ብድግ ብዬ ቀጥታ ሄድሁኝ ወደእነሱ ። ለመቆጣጠር የሚያዳግት የድፈቀው ድፈቀው ስሜት ተጨማመረብኝ። ወደ እነሱ ለመድረስ በጣም ጥቂት ሴንቲ ሜትሮች ሲቀረኝ ግን በአይኔ ብቻ ገልምጫቸው አለፍኩኝ። ዘበርጋ ሲያየኝ ክው ይበል አይበል ግን የተረዳሁት ነገር አልነበረም ።
ዘበርጋ ያለው የራብ አድማ መምታቴ ጉዳይ እውነት ነው ፤ በእርግጥም በኔ አልተጀመረም ። ብቻ ዘበርጋ በጣም ትልቅ ውሸት ነው የፈጠረው በምን የውስጥ ግፊት እንደዋሸ እና የዓይን ፍቅርን እንደምክንያት እንዳስቀመጠ በህግ ወይም በውግ መጠየቅን ባላስብም ነጭ የማይግልጠው ውሸት ነው የዋሸው።
በነጋታው አድማውን ለማቆም ወሰንኩኝ ምክንያቱም አድማው ሲጀመር ፤ በምን ምላሽ አድማዬን እንደማቆም በግልፅ አላሰብኩም ።
በእርግጥ አድማዬን ብቀጥል በረሐብ ተቆራምጄ ከመሞት እንደማልድን ይታወቃል ።
እስረኞቹ የረሀብ አድማ ሲመቱ ለመንግስት መልዕክት እያስተላለፉ ነው ። መንግሥት እስረኞችን እንዲበሉ ለማድረግ ጥያቄአቸውን መመለስ አለበት ።
እኔ ደግሞ ለማይሰሙኝ “ቲክቶዋርዲያን” ነው በአድማ መልክ ተቃውሞዬን ሳሰማ የሰነበትኩት። በነገራችን ላይ “ቲክቶዋርዲያን” የሚለው ቃል “ቲክቶክ” እና “ወራዳ” ከሚሉት ሁለት ቃላት የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም የተዋረደ ስራ የሚለጥፉ “የቲክቶክ ሰዎች” ማለት ነው።
በጣም ድብቅ የአካል ክፍሎችን ወደ ቲክቶክ ይፋ በማውጣት አድናቂዎችን ለማግኘት የሚደረገውን የሴቶች ያልተገባ ተገባርን በመቃወም የምቀጥል ቢሆንም የርሀብ አድማዬ ግን መቀጠል እንደሌለበት ወስኛለሁ ።
ቲክቶክ ላይ የማይሆን ነገር ማወዛወዝ ፣ የማይገለጥ ነገር መግለጥ ሊቆም ይገባል ።
ማስታወሻ : የርሀብ አድማ ከማቆሜ በፊት የቲክቶክ አካውንቴ ላይ የማውደም እርምጃ ወስጄአለሁ ።