” የዓይን ፍቅር የራብ አድማ የሚያስመታ ሆኖ ነው አሁን? ጥጋብ ነው እንጅ:: ” ሲል ተቀደደ። ድንግጥ አልኩ ።

ከ ወጉ የተወሰደ

ሰሞኑን አድማ እንደመታሁ የሰማ ሁሉ የየራሱን ሐሳብ መስጠት ይዟል ።

ሐሳብ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሥነ-ሥርዓቶች ቢቀመጡ ኖሮ እኔ ብቻ ነበርኩ አስተያየት ሰጪ ሆኜ የምገኘው ። ብቻ ይሉኝታውን ያጣ ሁሉ አስተያየቱን በአድማዬ ላይ ለክቦብኝ ያልፍ ይዟል ።

” ምን እባክህ…. ” ሲል ሰማሁት (ቀልቤ የማይወደው ከላባ ብጤ ነው) በሱ ቤት እሱ አይቶኛል እኔ አላያቸውም …

ሲያወራ ድምፁን መመጠን አይችልም ፣ ከጎኑ ላለው ጓደኛ ሳይሆን ከወንዝ ማዶ ላለ ሰው የሚያወራ ነው የሚመስለው ..

ብቻ የሆነ ሶሻል ሚዲያ ድምሰሳ ላይ የነበርሁ ቢሆንም ገታ አድርጌ መስማት ያዝሁ ።

” ምን ባክህ በርግጥ አድማ በእሱ አልተጀመረም .. ስንቶች ናቸው መንግስትን ተቃውመው የራብ አድማ የመቱት?.. ሰምተህ አታውቅም ? በዚያ ላይ ምክንያቱ በቂ አይደለም .. “

ከጓደኛው ‘እንዴት ?’ የሚል መልስ ቢጠብቅም አልተሳካም ። ራቁ ብዬ ስሰጋ ትንንሽም ቢሆን እንድሰማቸው በሚያስቸል ርቀት ሁለት ሰው ማስቀመጥ በምትችል የድንጋይ ወንበር ተቀመጡ !

” የዓይን ፍቅር የራብ አድማ የሚያስመታ ሆኖ ነው አሁን? ጥጋብ ነው እንጅ:: ” ሲል ተቀደደ።

ድንግጥ አልኩ ።

TikTok

“tiktok” አካውንቴን እያጠፋሁ የነበረ ቢሆንም፤ ለመደምሰሻ የሚሆን በቂ connection እና ትዕግሥት አልነበረኝም ።

የዓይን ፍቅር ነው አሉ ደሞ? አልሁ ለራሴ ለማልቀስ እና ለመቦከስ የተመቸ ስሜት ውስጥ ስደነቦቅ እየተሰማኝ።

ያንን ትልቅ ውሸት ከዋሸ በኋላ ከጓደኛው ምንም ምላሽ ባለማግኘቱ ቀጠለ…..

” አድማ መቀለጃ ይሁን ? የማንም ጥርቅም …. “

መታጋስ አልቻልኩም ብድግ ብዬ ቀጥታ ሄድሁኝ ወደእነሱ ። ለመቆጣጠር የሚያዳግት የድፋው ድፋው ስሜት ተጨማመረብኝ። ወደ እነሱ ለመድረስ በጣም ጥቂት ሴንቲሜትሮች ሲቀረኝ ግን በአይኔ ብቻ ገልምጫቸው አለፍኩኝ። ዘበርጋ ሲያየኝ ክው ይበል አይበል ግን የተረዳሁት ነገር አልነበረም ።

ዘበርጋ ያለው የራብ አድማ መምታቴ ጉዳይ እውነት ነው ፤ በእርግጥም በኔ አልተጀመረም ። ብቻ ዘበርጋ በጣም ትልቅ ውሸት ነው የፈጠረው በምን የውስጥ ግፊት እንደዋሸ እና የዓይን ፍቅርን እንደምክንያት እንዳስቀመጠ በህግ ወይም በውግ መጠየቅን ባላስብም ነጭ የማይግልጠው ውሸት ነው የዋሸው።

በነጋታው አድማውን ለማቆም ወሰንኩኝ ምክንያቱም አድማው ሲጀመር ፤ በምን ምላሽ አድማዬን እንደማቆም በግልፅ አላሰብኩም ።

በእርግጥ አድማዬን ብቀጥል በራብ ተቆራምጄ ከመሞት እንደማልድን ይታወቃል ።

እስረኞቹ የራብ አድማ ሲመቱ ለመንግስት መልዕክት እያስተላለፉ ነው ። መንግሥት እስረኞችን እንዲበሉ ለማድረግ ጥያቄአቸውን መመለስ አለበት ።

እኔ ደግሞ ለማይሰሙኝ “ቲክቶካርዲያን” ነው በአድማ መልክ ተቃውሞዬን ሳሰማ የሰነበትኩት። በነገራችን ላይ “ቲክቶካርዲያን” የሚለው ቃል “ቲክቶክ” እና “ወራዳ” ከሚሉት ሁለት ቃላት የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም የተዋረደ ስራ የሚለጥፉ “የቲክቶክ ሰዎች” ማለት ነው።

በጣም ድብቅ የአካል ክፍሎችን ወደ ቲክቶክ ይፋ በማውጣት አድናቂዎችን ለማግኘት የሚደረገውን የሴቶች ያልተገባ ተግባርን በመቃወም የምቀጥል ቢሆንም የራብ አድማዬ ግን መቀጠል እንደሌለበት ወስኛለሁ ።

ቲክቶክ ላይ የማይሆን ነገር ማወዛወዝ ፣ የማይገለጥ ነገር መግለጥ ሊቆም ይገባል ።

ማስታወሻ : የራብ አድማ ከማቆሜ በፊት የቲክቶክ አካውንቴ ላይ የማውደም እርምጃ ወስጄአለሁ ።