በእርግጥ ከጓደኛዬ የማደንቅለት ባህሪይው ሁሌም ከመብላቱ በፊት ሶስት ጊዜ በትምህርተ መስቀል አማትቦ ሲመቼው በግዕዝ አቡነ ዘበሰማያትን በሌላ ጌዜ በአማርኛ አባታችን ሆይን ደግሞ ነው ምግብ የሚጀምረው።
ከ ወጉ የተወሰደ
ብዙ ጊዜ ካፌ ከሰው ጋር መግባት አልወድም ። ለዚህ በዋናነት ሁለት ምክንያት የሚጠቀሱ ሲሆን ሌሎች ጥቃቅን ምክንያቶች አይኖሩም ለማለት አይቻለኝም ።
1ኛ ከልጅነት ጀምሮ የለመደብኝ ከሰው ጋር እየተያዩ መብላት የሚፀየፍ ባህሪዬ ነው።
በእርግጥ ሌሎች ተመጋቢዎች ቢኖሩም ቢያንስ እንኳ ከጓደኛ ጋር ባለመሄድ ዙሪያዬን አፅድቼ ደበቅ ወዳለች በታ ሄዶ ለመመገብ ይመቸኝ ዘንዳ ነው ብቻዬን እመርጣለሁ ።
2ኛ የአበላሌ ፍጥነት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ነው ለብቻ መግባትን የመረጥኩት ።
ይሉኝታ/ሼም የሚባል ችግር ስላለብኝ ምግቡን በጣም በትንሽ ደቂቃዎች ስመገብ እና አብረውኝ ያሉት ሲሳቀቁ እና ሲታዘቡኝ ለመጋፈጥ አልደፍርም ።
የሆነው ሆኖ ከአንድአንድ ቀን ቀን ይጥለኝና በሆነ አጋጣሚ ከጓደኞቼ ጋር መግባት ይከሰታል ።
አብዛኛውን ጊዜ ስሙን እገልጠው ዘንድ የማይቻለኝ ጓደኛዬ ጋር ካፌ እንገባለን ። ልጁ በካፌ ህይወት ውስጥ የማትረሳኝ ድንቅ የዜርፎር ፍቅር ልክፍት አለችበት ።
የዜርፎር ቀን ቀን አምስት ስዓት ማታ አስር ስዓት ጀምሮ ወደ ካፌ አካባቢ ሲንጎራደድ ይስተዋላል ።
በጣም ስለማያስችለው 5:30 /10:30 እስኪሆን ስራ መስራት ስለማይችል የካፌውን መከፈት 1 ሰዓት አስቀድሞ ማለትም ከ 5:00/10:00 ጀምሮ የሚጠባበቅ ምስኪን ነው።
ለስጋ ያለውን ፍቅር እና መስገብገብ ለታዘበ ሰው በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ስጋን የሚመገብ ይመስላል ።
በእርግጥ እኔም ከሱ ጋር መመገብ ስለለመድኩ ይሁን እንጃ ባላውቅም በማያስነቃ ሁኔታ 5:30/10:30 በጣም በጉጉት የመጠበቅ ልክፍት ተጠናውቶኛል። እንደውነቱ ከሆነ ዩንቨርስቲ ሳልገባ በፊት የበሬ ስጋ አልበላም ነበር ። የበግም ቢሆን የእለቱን ነው እንጂ ካደረ እና ከሰነባበተ አልይህ የምል አይነት ሰው ነበርኹ ። እዚ ከመጣሁ በኋላም ቢሆን ስጋ ወጥ በሚሆንበት ቀን ወጥ ማስደረግ እተው ነበር ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ምን እንደነካኝ ባላውቅም የዜርፎር ቀን ናፋቂ ሆንኩ። ካፌ ወጥ የሚያደርጉትን ሰዎች ሳይቀር በሚያደርጉልኝ የስጋ መጠን መመዘን ያዝሁ። ስጋ ሳያደርጉ የቀሩ እንደሆነ “አፈር ብይ” እል ዠመር በልቤ።
የሆነው ሆኖ እኔ እየተሸማቀቅሁም ቢሆን በድብቅ ስጋ በሚኖርበት ቀን ከዶርምም ይሁን ከላይብራሪ ወደ ካፌ የምወጣው ለካፌ መግቢያ 1 ስዓት ሲቀረው ነው።
አንድ ቀን እሁድ ከሰዓት በኋላ ላይብረሪ የገባሁት 6:00 ነበር ። አስር ስዓት ሲሞላ የካፌው ምግብ ድንገት ትዝ ብሎኝ ፣ ያላሰብኩትን ረሀብ ለቀቀብኝ ፤ የሚደብረው ደግሞ እሁድ ራት 11:00 ነው ካፌ የሚከፈተው ። ቢያንስ እንኳ እስከ 10:30 ላይብረሪ ለመቀመጥ ብሞክር አልቻልኩም ፤ ማንበቤን ገታ አድርጌ በስልኬ የሆነ ቪዲዮ ከፍቼ ሃሳቤን ለማባረር ብምክርም አልሆነም ። በመጨረሻም ከ ላይብረሪ ወጥቼ ሰው እንዳይታዘበኝ ከካፌው ራቅ ብዬ ስልኬን መጎርጎር ያዝኹ ፤ ሰዓት ሲደርስ ተፈናጥሬ ለመግባት የሚመች ቦታ ነው ።
ከደቂቃዎች በኋላ ያ ካፌ አብዛኛውን አብሮኝ የሚገባው ልጅ ከዋናው በር ሲመጣ አየሁት ። አረማመዱ ለመሮጥ ትንሽ የቀረው ነበር ፤ ለታዘበው ሰው መረዶ የተረዳ ወይ ሰው ሊያድን የሚሮጥ እንጅ ለሆዱ አይመስልም ።
ጥድፊያው ወደ ካፌ ለመሄድ እንደሆነ አልጠፋኝም።
እኔ በካፌው መሄጃ መንገድ በኩል ስለነበርኩ እኔ ጋ ሲደርስ ፈገግታ አሳይቶኝ ፣
” ኧ ሶባ እንሂዳ..? ” አለኝ።
” እንዴ ገና 10:25 እኮ ነው? ” አልኩት ስልኬን እያየሁ ።
” እና 10:30 እኮ ይከፈታል 5 ደቂቃ እኮ ነች የቀረች … ” አለኝ አንድ እርምጃ ራመድ ብሎ ከሄድክ እንሂድ ካልሆነ ተጠንቀር በሚል አይነት ፊት።
” ኧረ አንተ ሰው እሁድ ነው እኾ!! ” አልኩት እየሳቅሁ ።
ዱብዳ ነበር የሆነበት ፤
” ኤጭ ረስቼዋለሁ በናትህ ” አለኝና አብሮኝ ተቀመጠ ።
በእርግጥ ከጓደኛዬ የማደንቅለት ባህሪይው ሁሌም ከመብላቱ በፊት ሶስት ጊዜ በትምህርተ መስቀል አማትቦ ሲመቼው በግዕዝ አቡነ ዘበሰማያትን በሌላ ጌዜ በአማርኛ አባታችን ሆይን ደግሞ ነው ምግብ የሚጀምረው።
እኔም በዚህ አልታማም አቡነ ዘበሰማያት ይትቀደስ ስምከ ትምጣ መንግስትከ……..
….. ኢታባነ እግዚኦ ውስተመንሱት..
ወይም
አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግስትህ ትምጣ……………..
……. አቤቱ ወደፈተና አታግባን ……
ሳልል አልመገብም።
ስንቆራጠጥ ቆይተን ሰዓቱ ደርሶ ካፌ ገባን ። በጣም ቀደም ስላልን የመጀመሪያዎቹ ባንሆንም ብዙ ተማሪዎች አልነበሩም ። ከፊት ለፊቴ የነበረው ጓደኛዬ ፤ የሚገራርሙ የስጋ ዘላላዎች ሲደረግለት ተመለከትኩ ፣ ማጋነን እንዳይሆን እንጂ ወጥ ብዙም አልነበረውም። የስጋ ጋጋታ ።
በርግጥ በጀርባው ስለነበርኩ ለጨላፊዋ ያሳያትን ፈገግታ አልተጋራሁትም ። በስጋው ብዛት መደናበሩ የገባኝ ከተደረደሩት የኩባያ ውሃዎች ሳያነሳ ወደ ተለመደችዋ መቀመጫችን ሲራመድ ነው። እኔም ሁለት ኩባያዎችን ይዤ ከዃላው ስከተለው አንዴ ሲያማትብ አየሁት። ከተል ብዬ ስሄድ እርምጃውን ቀንሶ አንገቱን አቀርቅሮ እየተራመደ ስለነበር ከኔ የአረማመድ ፍጥነት ስላልተመጣጠነ ቀደም ብዬው አለፍኩና ቦታችን ከመቀመጤ ወዲያው ደረሶ ፊትለፊቴ ተቀመጠና መመገብ ጀመረ።
” አይ ይሄ ስጋ …. ፆሎቱ ቀረ ” አልኩ በልቤ የአቡነ ዘበሰማያት ፀሎቱን እንደረሳ ወይ ቼል እንዳለው ተረድትቼ።
ያመጣሁለትን ውሃ ጠጋ ሳደርግለት፦
” ኧረ በለው ረስቼው መጥቼ ነው ” አለኝ ሀፍረት እየተሰማው ።
እኔም ከኋላው ስከተለው ምግቡን እንደያዘ እየተራመደ ያማተበው ፣ አቀርቅሮ የተራመደው ትዝ አለኝና
” ምነው ወደዚህ ስትመጣ አማተብህ ምን አይተህ ነው? ” አልኹት።
አንድ ሁለቴ ከስጋው ነጬና….
” ኧረ ምንም አላየሁም እዚ ተቀምጬ ጊዜ ከማቃጥል በመንገድ አባታችን ሆይ ልበል ብዬ እኮ ነው ፤ ቀስ እያልሁ ስለመጣሁ እዚ ስቀመጥ አባታችን ሆይን ጨርሼው ነበር!! ” አለኝ …
የዚያን ቀን የሳቅሁትን ሳቅ መቼም አልደግመውም ።