እንደሌላው ለጊዜ ማሳለፊያ ፤ ወይ ደሞ እኛ ሰፈር ሲሉት እንደሰማሁት ድርሻዬን ለማንሳት ሳይሆን፤ አልያ ደሞ ሀቅም ወይ ውበት አይቼ ሳይሆን፤ ሳላልመዉና ሳላቅደው ፍቅር የተሰኘ አዚም በወረርሽኝ መልክ ድንገት ተጠናወተኝ። “እኔን ፍቅር ሊይዘኝ?” አያልሁ እለፍፍ እንዳልነበር ሁሉ ከሷ ውጪ ማሰብ ማለም ይሳነኝ ገባ።

እኔ በዘመኑ ፍቅር እምነት ስላልነበረኝ ፍቅርን ከአካባቢዬ ለማራቅ ሶስት ስልቶች ነበሩኝ። መከላከል ፣ መጋፈጥ እና መቀበል ።

መከላከል ማለት ፍቅር የሚጠነሰስበትን አጋጣሚ ከነጭራሹ አለመፍጠር ማለት ሲሆን ሴት ባለበት ሁሉ ባለመድረስ ከደረሱም ስለነሱ መጥፎ ነገር በማሰብ ፍቅርን ለማጨናገፍ ጥረት በማደረግ ይተገበራል ። መከላከል ካልተሳካ ወደ መጋፈጥ እሔዳለሁ ።

መጋፈጥ ደግሞ ፍቅር ሊይዝ ሲታገል አሸንፎ ፍቅርን በማዳከም ከፍቅር ነፃ መውጣት ነው ። ያ ማለት ከሴቷ ስህተት ወይ ድክመት በመፈለግ በአእምሮ ውስጥ ፍቅር እንዲመነምን ማድረግ ነው። አለባበሷ፣ ጓደኞቿ ፣ ከዚህ በፊት የነበራት ህይወት ፣ ወይም ደግሞ ንፅህናዋን በማሰብ ከሴት ጋር ለመዳራት እድል አለመስጠት ነዉ።

ሶስተኛው መቀበል ደግሞ ፍቅር ውስጥ ለመዘፈቅ መምረጥ ግን ከዓላማ ሳያፈነግጡ በአንድ ጎን ፍቅርን በአንድ ጎን ደግሞ ትምህርትን ማስቀጠል ነው ።

የሶስተኛው ምርጫ በፍጹም ይከሰታል የሚል ሐሳብ በፍጹም አልነበረኝም ። “ሀይ” በሚል ፅሁፍ ተጀናጅና ክብሯን አሳልፋ ለምትሰጥ፣ ባህሏን፣ ንፁህ አስተሳሰቧን እና ይሉኝታዋን ለምተሸጥ፤ ጨለማን ተገን አድርጋ ከወንድ ጋር ለምትንሸራሸር የዘመኗ እንስት እጄን አልሰጥም የሚል ድንቅ አቋም የነበረኝ ሰው ነበርኩ ።

ዛሬ ላይ ግን ነገር ሁሉ ተለወጦ አይቸው የማላውቀው ከደስታም ከሃዘንም ሊመደብ የማይችል ስሜት መንፈሴን ተቆጣጠረው ። በምን እንደሆነ ሳላውቅ የመጀመሪያውን የፍቅር መከላከያ ስትራቴጂ ሳልጠቀም ፍቅር ካልያዝሁህ ብሎ ሰላም እየነሳኝ ባለበት የሁለተኛውን ስትራቴጂ መጠቀም ያለብኝ ሰዓት እራሴን አገኘሁት ።

ምክንያት እየፈለግሁ እሷ ባለችበት ሳላስነቃ ማለፍ፤ እሷን እያሰብኩ የሙገሳ ግጥሞችን መድረስ ፤ እሷ የተለየች እንደሆነች አድርጎ ማሰብ ውስጥ ተነክሬ እራሴን አገኘሁት ።

የሁለተኛ የፍቅር መከላከያ ስትራተጂን መተግበር ጀመርኩ ። አለባበሷን፣ አነጋገሯን፣ ውሎዋን ፣ አስተሳሰብና ጓደኞቿን አጤንኋቸው ። ሁሎችም እኔ የማልፈልጋቸውን አይነት ናቸዉ ነገር ግን አልቻልኩም ከሷ ውጭ ያለው አለም ጨልሞ ታየኝ። ሁለተኛው ስትራቴጂም አልተሳካልኝም እራሴን በጣም ስለተጠራጠርኩት ለሰባት ቀናት በሌሊት ፀበል እየሄድኩ ተጠመቅሁ ለውጥ አልመጣም ።

ሁሉ ነገሯን ሳልወደው እሷን ወደድኳት ፍቅር ተሰዶ አስተሳሰብ እና ከካላቴ ውስጥ ገባ። ፍቅሬን ለሷ መንገር እንዳለብኝ ተሰማኝ ምክንያቱም ትኩስ ምግብ በአፍ ይዞ መቆየቱ መላላጥን ያስከትላልና ወደ ሆድ መላክ አለበት ።

ምን እንደምላት በማሰብ እና ወኔ ለማመንጨት በሚል ለአራት ቀናት ከትምህርት፤ ለ ሁለት ቀናት ከክላስ እራሴን አገለልኩ።

ቅዳሜ ከኋላዋ ተከትዬ አጭር የወረቀት ላይ መልዕክት በሰው ላክሁላት።

“ሰላም ላንች ይሁን። የሞትና የህይወት ጉዳይ የሆነ አንድ ነገር ልነግርሽ እፈልጋለሁና እንደምንም ብለሽ እሁድ 12 ሰዓት ኳስ ሜዳው አካባቢ ብቻሽን ነይ እጠብቅሻለሁ።”

ይላል ደብዳቤው ።

ጠዋት ደብዳቤውን ከላክሁላት በኋላ 3 ረጃጅም እሁዶች የሚያክል ሰዓት ስጨነቅ ስጠብ ዋልኩኝ። 12 ሰዓት ሲሆን ፍራቻዬ ጨመረ። አትመጣ ይሆን ? ምን ልልላት ነው? ወዴት እየሄድኩ ነው ግን? የሚሉ እጅግ የሚያደነቁሩ ጥያቄዎች ይደራረቡብኝ ያዙ።

ስፈራ ስቸር 12:15 አለ ረዝሞ የዋለው ቀን ይሮጥ ያዘ ወደ ቀጠሮዬ አመራሁ።

ወደ ኳስ ሜዳው ስደርስ አካባቢው ያለወትሮው ፀጥታ እና ሰው ማጣት ገጥሞታል ። አካባቢውን ስቃኘው አንድ ሰው አየሁ ፍርሐቴ እጅግ እየጨመረ ሄደ እሷ እንደሆነች ውስጤ በእርግጠኝነት ያስባል ።

ድንገት የተቀመጠችዋ እንስት ያለወትሮዋ ነጭ ቀሚስ የለበሰች ፤ ፀጉሯ በጀርባዋ ተነስንሶ የሚታይ ሆና ታየችኝ ። ከተቀመጠችበት ተነስታ ወደ ሰልኳ አቀርቅራ ታየችኝ ። ለሰላሳ ደቂቃ አካባቢ ጠብቃ ስቆይባት ለመሔድ መነሳቷ ነው ብየ አሰብኩ። በፍርሃት እየተናጥሁ በኋላዋ በኩል ተጠጋሁ ። በጣም ጥቂት ርቀት ሲቀረኝ እና እሷ መሆኗን ሳረጋግጥ ፥

“ስላረፈድኩ ይቅርታ” አልኳት እንደምንም ጉልበት አሟጥጬ ።

“ባላደብዳቤው ነህ ?” አለችኝ ወደኔ ዙራ ሳትጨረስ ።

“እ እ.. ኧ እ” መናገር ተቸገርኩ ።

ቀና ብሎ አይኗን የማየት ድፍረት አጣሁ ከአስተሳሰቤ ፣ ከህይወት ህጌ ማፈንገጤ በሃሳቤ ተወራጨብኝ። በህይወቴ ሴትን ለፍቅር ተመኝቼ አላውቅም እስከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን ሴትን ልጅ መቅረብ እና አብሮ መታየት አልችልም ነበር ። ሴትን መዳሰስ ፣ ማቀፍ እና መሳም አድርጌም ፣ተመኝቼም ፣ አስቤም አላውቅም። ሴት ከአላማዋ ስትሰናከል ፣ በፍቅር ስም የክብር መገለጫዋን ድንግልና ለማይገባው ስትለግስ፣ በየተራራ፣ በየጥሻውና ሜዳው እንደ እንስሳ ስትላላስ ስትውል ያመኛል ።

እኔ ሴትን እንኳን እንደፍቅረኛ ብይዝ ልጠብቃት፣ ልንከባከባት ፣ አይኗን አይቼ ደስ ሊለኝ እንጅ ልረካባት፤ልዝናናባት አይደለም የሚል እምነት ያለኝ እና የነበረኝ ሰው ነኝ። እና ከፊቷ ቁሜ እንደረከሱት ልረክስ፤ በሴት ፍትወት ስጋ እንዳገኙ እኔም እሱን ልፈፀም እንደሆነ ተሰማኝ። ማንነቴ አካሌን ፣ ምኞቴን፣ አመንዝራነቴን አይቶ ሲያለቅስ በዓይነ ልቦናየ ታዬኝ ቀና ብዬ ላያት ተቸገርኩኝ ። እሷን ሳይሆን ክህደቴን ፈራሁት ። ማንነቴን መካዴ ፣ የተቸኋቸው ያደረጉትን ነገር ላደርግ ፣ ጀንጅኜ ሴት ላሳምን እየታገልሁ ያለሁበትን ሁኔታየን ፈራሁት ።

በሃሳብ ውስጥ እንደገባሁ እና ፍርሐቴን ተረድታ ይመስለኛል፥

“ትንሽ ወደዛ አካባቢ ዝቅ እንበልና እናውራ?” አለችኝ ወደቦታው እየጠቆመች።

“እሺ” አልኹ

ከኳስሜዳው ከፍ ካለ ደረጃ ወደታች ወደሜዳማው መሬት መውረድ እንደጀመርን ድንገት ምኑ እንዳናቀፈኝ ሳላውቀው ከደረጃው ቁልቁል ተወርውሬ በፊቴ ተደፋሁ።

“ወይኔ”

የሚል የተፈቃሪዬ የድንጋጤ ድምጽ ከሩቅ ቦታ እንደመጣ የገደል ማሚቶ ሆኖ ተሰማኝ። ተፈቃሪዬ ተደናግጣ ወደኔ ደፋ ስትል ታየኝ

“ኧረ አይንህን ግለጥ እባክህ እሱባለው ፣ ኧረ እሱቤ!?፣ ተጎዳህ እንዴ!?፣ አይንህን ግለጥ”

የሚል ድምፅ ይሰማኛል ። አይኔን ለመግለጥ ተቸገርኩ ። አሁንም ጥሪው ቀጠለ፣

“እሱባለው አይንህን ግለጥ እባክህ?፣ ተነስ እንጂ አይንህን ግለጥ”

እንደምንም አይኔን ስገልጠው እራሴን ከዶርማችን ወለል ተዘርሬ በድንጋጤ በተዋከቡ የዶርማችን ተማሪዎች ተከብቤ አገኘሁት ።

“ምንድነው ፣ ምን ሆኜ ነው ?” አልኹኝ የከበቡኝን በመወናበድ እያማተርሁ ።

ጥያቄየን በመመለስ ፈንታ፥

“አይዞህ፣ አይዞህ እዚ ጋ ተቀመጥ” እያሉ ደጋግፈው አስቀመጡኝ።

ከ 10 ደቂቃ በኋላ ከአልጋዬ ላይ ወደ ወለል መውደቄ ግልጽ ሆነልኝ ከ ሌላ 20 ደቂቃ በኋላ ጎኔ ፣ ደረቴ ፣ ሆዴ እና ጀርባዬ መጠነኛ ጉዳት ማስተናገዱን ተረዳሁ ከሌላ 30 ደቂቃ በኋላ ማንነቴና አሰተሰሰቤ ሁሉ እንደነበረ መሆኑን ተገነዘብኩ ።

እሱባለው ቸኮል